የአፍሪካ ሀገራት የአስትራዜኔካ የኮቪድ-19 ክትባትን መጠቀም ሊቀጥሉ ይገባል- አፍሪካ ሕብረት
የአውሮፓ ሀገራት ክትባቱን እንጠቀም እና አንጠቀም በሚል ለሁለት መከፈላቸው ይታወቃል
ሕብረቱ “ክትባቱ ሊያስከትለው ይችላል ከተባለው አደጋ ይልቅ ጥቅሙ ያይላል” የሚል እምነት አለው
የአፍሪካ ሀገራት የአስትራዜኔካ የኮቪድ-19 ክትባት መጠቀምን እንዲያስቀጥሉ የአፍሪካ ሕብረት ጠየቀ፡፡
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል (ሲ.ዲ.ሲ) ዋና ዳይሬክተር ጆን ንከንጋሶንግ “ሕብረቱ የዓለም ጤና ድርጅት ሀሳብን እንደሚጋራና ክትባቱ ምናልባትም ሊያስከትለው ይችላል ከተባለው አደጋ ይልቅ ጥቅሙ ያይላል፤ ስለሆነም የአፍሪካ ሀገራት ክትባቱን መስጠት ሊያስቀጥሉ ይገባል” የሚል እምነት አለው ብለዋል፡፡
ከክትባቱ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ነገሮች ሲ.ዲ.ሲ በየጊዜው ጥብቅ የክትትል ሪፖርት ይኖረዋልም ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
የአህጉሪቱ ሕብረት ይህን መሰል ምክረ-ሀሳብ የሰነዘረው፡ ክትባቱ “የደም መርጋትን ያስከትላል” መባሉን ተከትሎ በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት መካከል ልዩነት በተፈጠረበት እና ከ10 በላይ ሀገራት ክትባቱን ባቋረጡነት ወቅት ነው፡፡
በአህጉረ አውሮፓ ክትባቱ ሊሰጥ ይገባል እና ሊሰጥ አይገባም የሚል ከፍተኛ ልዩነት ያለ ሲሆን እንደ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስፔንና ጣሊያን የመሳሰሉ ሀገራት የአውሮፓ ህብረት ክትባቱ ምንም ችግር የለውም የሚል ሪፖርት ካላቀረበልን ክትባቱን አንጠቀምም ብለዋል፡፡
ሌሎች ደግሞ ከትባቱን ብንጠቀመው መልካም ነው የሚል የልዩነት ሀሳብ ያላቸው ሲሆን ለህዝባቸው ክትባቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ ሮይተርስ እንደዘገበው፡፡