“አስትራ ዜኒካ ክትባት ደም መርጋትን ያስከትላል ስለመባሉ ምንም ማረጋገጫ የለም”- የዓለም ጤና ድርጅት
የደም መርጋት ችግሩ እስካሁን በ40 ሰዎች ላይ ተከስቷል
በአውሮፓ እስካሁን 17 ሚሊየን ገደማ ሰዎች አስትራ ዜኒካ ክትባትን ወስደዋል
አስትራ ዜኒካ የተባለው የኮቪድ-19 ክትባት ደም መርጋት ችግርን እያስከተለ ነው በሚል በርካታ የአውሮፓ ሀገራ ክትባቱን መስጠት እያቆሙ ይገኛሉ።
እስካሁንም ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ አየርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኦሰትሪያ፣ ቡልጋሪያ፣ አይስላንድ እና ኖርዌይ ክትባቱ በሀገራቸው እንዳይሰጥ ከልክለዋል።
በጉዳዩ ላይ የተጠየቀው የዓለም ጤና ድርጅትም ከአስትራ ዜኒካ ክትባ ጋር ተያይዘው እየወጡ ያሉ ሪፖርቶችን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ከርስቲያን ሊንድሚየር፤ ድርጅቱ ስለ ጉዳዩ ሙሉ መረጃ እንዳለው ገልጸው፤ ወደ ፊት የሚለወጥ ነገር ካለ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
“ክትባቱ የጤና እክሎችን እያስከተለ ነው” ስለመባሉ እስካሁን ምንም የተረጋገጠ ማስረጃ እንደሌለና የክትባት ዘመቻው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።
በደም ምርጋቱ ዙሪያ ጥናት እደረገ ያለው የአውሮፓ ጤና ማህበር በበኩሉ ክትባቱ መሰጠቱ መቀጠል አለበት ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
የብሪታንያ የመድሃኒት ቁጥጥር አካላትም ክትባቱ የደም መርጋቱን ስለማስከተሉ የተረጋገጠ ምንም ዐይነት ማስረጃ እንደሌለ በማሳሰብ ህብረተሰቡ ክትባቱን መውሰዱን እንዲቀጥል መክረዋል።
በአውሮፓ እስካሁን 17 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ክትባቱን ወስደዋል፡፡ ደም ምርጋቱ ከ40 ባልበለጡ ሰዎች ላይ እንዳጋጠመም ነው የተነገረው።
ኢትዮጵያ “ክትባቱ በትክክል የተባለውን ችግር እንደሚያስከትል በጥናት የተረጋገጠ ነገር የለም” ማለቷ ይታወሳል፡፡
ከሳምንት በፊት ሃገር ውስጥ የገባው የአስትራ ዜኔካ ክትባት መስጠቱ ይቀጥላል ሲል የጤና ሚኒስቴር በተለይ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጸ መዘገቡም የሚታወስ ነው።