ፕሬዚዳንቱ ክትባቱን በቅድሚያ የወሰዱት በክትባቱ ላይ ያላቸውን መተማመን ለማሳየት ነው
ሶማሊያ የኮቪድ 19 ክትባን በዛሬው እለት ለዜጎቿ በይፋ መስጠት መጀመሯ ተነግሯል።የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆም ክትባቱን በቀዳሚነት በመውሰድ የክትባት ዘመቻውን በይፋ አስጀምረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ክትባቱን በቤተ መንግስት መገናኛ ብዙሃን በተገኙበት የወሰዱ ሲሆን፥ ይህም በክትባቱ ላይ ያላቸውን መተማመን ለማሳየት ነው ተብሏል።
የጤና ባለሙያዎች፣ እድሜያቸው የገፉ እና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ክትበቱን በቅድሚያ እንደሚያገኙም የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሶማሊያ በኮቫክስ አማካኝነት 300 ሺህ የኦክስፎርድ አስትራ ዜኒካ ክትባቶችን በትናንትናው እለት መረከቧ ይታወሳል።
15 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሶማሊያ 20 በመቶ ዜጎቿን ለመከተብ የሚስችላትን በቂ ክትባት በኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት ለማግኘት እቅድ እንዳላት የሀገሪቱ መንግስት መግለጹን የሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘገባ ያመለክታል።