ኢትዮጵያ የአስትራዜኔካ ክትባትን መስጠት እንደምትቀጥል ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ
በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የደም መርጋት ችግር ያስከትላል በሚል ክትባቱ እንዲቋረጥ አድርገዋል
ከክትባቱ ጋር ተያይዞ በኢትዮጰያ እስካሁን የገጠመ ችግር የለም ሲሉ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ከክትባቱ ጋር ተያይዞ እስካሁን የገጠመ ችግር የለም ብለዋል፡፡
የትኛውም ክትባት መጠነኛ የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖረው ይችላል ያሉት ዶክተር ሊያ፣ በተከተቡትና ባልተከተቡት መካከል እምብዛም ልዩነት የለም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከአስትራዜኔካ ክትባት ጋር ተያይዞ ወደ ፊት አዲስ ነገር ካለ እናሳውቃለን ያሉት ሚኒስትሯ፣ ከክትባቱ ጋር ተያይዞ እስካሁን የገጠመ ችግር ባለመኖሩ ክትባቱን መስጠታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡
ክትባቱን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠርና ብዥታዎችን ለማጥራት የማስተማሪያ ግብዓቶች በተለያዩ ቋንቋዎች እየተዘጋጁ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
ጀርመን ፣ ፈረንሳይ ፣ ጣሊያን እና ስፔንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የደም መርጋት ያስከትላል በሚል ስጋት አስትራዜኔካ የተሰኘው ክትባት እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትም ከአስትራ ዜኒካ ክትባ ጋር ተያይዘው እየወጡ ያሉ ሪፖርቶችን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
“ክትባቱ የጤና እክሎችን እያስከተለ ነው” ስለመባሉ እስካሁን ምንም የተረጋገጠ ማስረጃ እንደሌለና የክትባት ዘመቻው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው ድርጅቱ ትናንት በቃል አቀባዩ በኩል ያስታወቀው፡፡
በደም መርጋቱ ዙሪያ ጥናት እያደረገ ያለው የአውሮፓ ጤና ማህበርም ፣ ክትባቱ መቀጠል አለበት ብሏል፡፡