በ2025 ጠንካራ ወታደራዊ ሀይል ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት
መልክዓምድራዊ አቀማመጥ፣ የጦር መሳሪያ አቅም እና የወታዳራዊ ዕዞች ብዛት ደረጃውን ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋሉ መስፈርቶች ናቸው
ግብጽ በአፍሪካ ጠንካራ ጦር ያላት ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ለመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ መመደብን ይፈልጋል፤ የመከላከያ በጀት የላቀ የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ፣ መሠረተ ልማትን ለማዘመን እና ወታደራዊ ስልጠናዎችን በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በአፍሪካ አህጉር በተለያዩ ሀገራት መንግስትን ከተቆጣጠሩ ወታደራዊ አመራሮች ባለፈ በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ሀገራት በውስጥ ቀውሶች እየተናጡ ነው፡፡
እነዚህ ተግዳሮቶች በሀገሮች አለመረጋጋት በመፍጠር የጅምላ መፈናቀልን አስከትለዋል፡፡
መሰናክሎቹን ለመቅረፍ እንደ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ በኢኮኖሚ የተረጋጉ ሀገራት በመከላከያ ሰራዊታቸው ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የተሻለ የጦር መሳሪያ እና የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወታደሮቻቸውን ለማስታጠቅ አስፈላጊው መሣሪያና ግብአት የሌላቸው ሀገራት ከእነርሱ በተሻለ በገንዘብ የሚደገፉ አሸባሪዎች እና ታጣቂዎችን እየታገሉ ይገኛሉ፡፡
የአፍሪካ ወታደራዊ አቅም ከጥቂት አመታት ወዲህ መሻሻሎችን እያሳየ ቢሆንም፤ የአህጉሪቱ ወታደራዊ አቅም አሁንም ካደጉት ሀገራት በእጅጉ ኋላ የቀረ መሆኑን የግሎባል ፋየር ፖዎር ኢንዴክስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ልዩነቶቹ የበጀት ድልድል፣ የቴክኖሎጂ እድገት፣ ስልጠና፣ የሀገር ውስጥ መከላከያ ኢንዱስትሪዎች፣ ስልታዊ አቅም እና የትብብር ግንባታ አቅሞችን በመሳሰሉ ቁልፍ ዘርፎች የሚታዩ ናቸው፡፡
እንደ ግሎባል ፋየር ፓወር ሪፖርት የአንድ ሀገር ወታደራዊ ጥንካሬ የሚገመገመው በወታደራዊ እዞች ብዛት፣ የበጀት መጠን፣ የሎጂስቲክስ አቅም እና በመልክዓምድራዊ አቀማመጥ እና ሌሎችም መነሻዎች ነው፡፡
በዚህ መለኪያ መሰረት በ2024 በአለም 15ተኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ግብጽ በተያዘው 2025 አመት ወደ 19ኛ ደረጃ ብትንሸራተትም ከአፍሪካ በወታደራዊ አቅም አንደኛነቷን አስጠብቃለች፡፡
ግብጽን በመከተል በአመት ለመከላከያዋ 25 ቢሊየን ዶላር የምትመድበው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ሲይዙ በአለም 52ተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በአፍሪካ 5ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በአንጻሩ በ2025 ደካማ ወታደራዊ አቅም ካላቸው አፍሪካውያን ሀገራት መካከል ቤኒን ፣ ሶማሊያ ፣ ሴራሊዮን ፣ ላይቤሪያ እና ጋቦንን የመሳሰሉ ሀገራት ተካተዋል፡፡