ከአፍሪካ አልጀሪያ እና ሞሮኮ ከፍተኛ የጦር በጀት በመመደብ ቀዳሚ ናቸው
ሃያላን ሀገራት ጦራቸውን ለማጠናከር በየአመቱ የሚመድቡት በጀት እየጨመረ መሄድ ፉክክራቸውን እያሳደገ አለምን የባሰ ውጥረት ውስጥ እየከተተ ነው።
ጠንካራ ጦር የገነቡት አሜሪካ እና ቻይና በያዝነው 2025 የመደቡት ወታደራዊ በጀት ካለፈው አመት ዝቅ ያለ መሆኑን የሀገራትን ወታደራዊ አቅም ደረጃ የሚያወጣው "ግሎባል ፋየርፓወር" አስታውቋል።
ዋሽንግተን እና ቤጂንግ የአለም ሀገራት በድምሩ ለጦራቸው ከሚይዙት በጀት ውስጥ ግማሹን (ከ1 ነጥብ 2 ትሪሊየን ዶላር በላይ) ይመድባሉ።
አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቆም የሚሹትና ጦርነቱን አስቆማለሁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይትሃውስ ዳግም መመለስ የፔንታጎንን በጀት እንዲቀንስ ሊያደርገው ይችላል ተብሏል።
ከዩክሬን ጋር ጦርነት ላይ የምትገኘው ሩሲያ በበኩሏ የ2025 ወታደራዊ በጀቷን በ25 በመቶ ማሳደጓን መግለጿ ይታወሳል።
ሀገራት ለመከላከያቸው የሚይዙትን በጀት በግልጽ ይፋ እንደማያደርጉ ያወሳው ግሎባል ፋየርፓወር ከተለያዩ ምንጮች ያጠናቀረውን አሃዛዊ መረጃ መሰረት አድርጎ ህንድን ከፍተኛ የጦር በጀት ከሚይዙ ሀገራት በአራተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
በ2025 ጦሯን ለማጠናከር 74.7 ቢሊየን ዶላር የያዘችው ሳኡዲ አረቢያ ደግሞ ብሪታንያ፣ ጃፓን እና አውስትራሊያን ታስከትላለች ነው ያለው ድረገጹ።
ፈረንሳይና ዩክሬን ደግሞ 9ኛ እና 10ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን፥ አፍሪካዊቷ አልጀሪያ 25 ቢሊየን ዶላር በመመደብ ከ145 ሀገራት 21ኛ ደረጃን ይዛለች።
በግሎባል ፋየርፓወር መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ 2.097 ቢሊየን ዶላር በመመደብ 71ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የደቡብ እስያዊቷ ሀገር ቡሃታን በ14 ሺህ ዶላር አመታዊ ወታደራዊ በጀት የመጨረሻውን ደረጃ መያዟ ተጠቁሟል።