ለተመድ ሰላም ማስከበር ዘመቻ ከፍተኛ ወታደር የላኩ የአፍሪካ ሀገራት
የእርስ በርስ ግጭትና ሽብርተኝነት ባየለባቸው የአፍሪካ ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላም አስከባሪዎች ተሰማርተው ይገኛሉ
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ግጭት ባለባቸው ሀገራት ፈቃድ የሰላም አስከባሪ ሀይሎችን ያሰማራል
ጥቂት በማይባሉ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ልዩነት ፣ የስልጣን ፍላጎት ፣ ኢፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እና ሽብረተኝነት የፈጠሯቸው ግጭቶች ሰላምን አናግተዋል፡፡
እነዚህ ለአመታት የዘለቁ ብጥብጥ እና ጦርነቶች የሀገራቱን ሰላም ከማደፍረስ ባለፈ የህዝቦችን መከራ በማብዛት በኢኮኖሚ ወደ ኋላ እንዲቀሩ እና ዜጎች በድህነት እንዲማቅቁ ምክንያት ናቸው፡፡
በሀገራቱ እውቅና ያለውን መንግስት ለመጠበቅ እና ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ሀይሎችን ከተለያዩ ሀገራት በማውጣጣት ማሰማራት ከጀመረ አስርተ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
የሰላም አስከባሪ ሀይሎች በቀጥታ በግጭት ውስጥ ከመሳተፍ ይልቅ ቀለል ያሉ የጦር መሳርያዎችን በመታጠቅ ብጥብጥን ለማርገብ እና መንግስታት ሀገራቸውን ሙሉለሙሉ መቆጣጠር እንዲችሉ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የሚያስማራቸው እነኚህ ሀይሎች በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአለም ክፍሎችም ባለፉት አመታት ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሶማሊያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ጦሯን በማሰማራት በሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ላይ በመሳተፍ ከሚጠሩ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡
በተለይ አልሸባብን ለመዋጋት ለ17 አመታት በሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በማሰማራት በሰላም ማስከበር ዘመቻው ጉልህ ሚና ተጫውታለች፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2024 በሰላም ማስከበር ደረጃዎች በርካታ ቁጥር ያለው ወታደሮችን ያዋጡ የአፍሪካ ሀገራትን ዝርዝር ባወጣበት መረጃው ሩዋንዳን በቀዳሚነት አስቀምጧታል፡፡
5918 ጦሯን ለሰላም ማስከበር የሰጠችው ሀገር በአፍሪካ አንደኛ ስትሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በሶስተኛነት ትገኛለች፡፡
1513 ወታደሮቿን ያሰማራችው ኢትዮጵያ ደግሞ ከአፍሪካ 6ተኛ ከአለም ደግሞ በ12 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡