ኢትዮጵያ ፖሊሶች ጉቦ ከሚቀበሉባቸው የአፍሪካ ሀገራት ስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?
አፍሮባሮሜትር በ39 ሀገራት የፖሊሶችን የሃይል አጠቃቀም፣ የሙስና እና ሌሎች ወንጀሎች ተጋላጭነት የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል
ጥናቱ ፖሊሶች ሙያዊ መርህና የዜጎችን መብት አክብረው እንደሚንቀሳቀሱ የሚያምኑ አፍሪካውያን 30 በመቶው ብቻ ናቸው ብሏል
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየአመቱ በሚያወጣው የሀገራት የሙስና ተጋልጭነት ደረጃ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ዴሞክራሲ በራቃቸውና ፍትህ ማስፈን ባልቻሉ ሀገራት የዜጎችን በሰላም ወጥቶ መግባትና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርን የማረጋገጥ ሃላፊነት የተጣለባቸው ፖሊሶች ጭምር የችግሩ አካል ሆነው ይታያሉ።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ሙስናን ለመዋጋት ህጎችን ቢያወጡም ተፈጻሚ በማድረጉ ሂደት በርካታ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል።
አፍሮባሮሜትር የተሰኘው ድረገጽ በ39 ሀገራት የፖሊሶችን የሃይል አጠቃቀም፣ የሙስና እና ሌሎች ወንጀሎች ተጋላጭነት በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል።
ከ2021 እስከ 2023 የተካሄደው ጥናት ፖሊሶች ሙያዊ መርህና የዜጎችን መብት አክብረው እንደሚንቀሳቀሱ የሚያምኑ አፍሪካውያን 30 በመቶው ብቻ ናቸው ብሏል።
54 በመቶ አፍሪካውያን ከፖሊሶች ድጋፍ ለማግኘት ቀላል መሆኑን ሲገልጹ፥ 36 በመቶው ጉቦ መክፈል ግዴታ ነው ማለታቸውም በጥናቱ ተመላክቷል።
ይህም ፖሊሶች በህብረተሰቡ ዘንድ ታማኝነታቸውን እየሸረሸረ በሙያው ላይም አሉታዊ አመለካከት እንዲዳብር ማድረጉ ነው የተገለጸው።
በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የወንጀል ጥቆማዎችንና ድንገተኛ አደጋን ሪፖርት አድርጎ ፈጣን የፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ብሎም በወንጀል የሚያስጠረጥር ጉዳይን ለማስቀረት ጉቦ መክፈል እየተለመደ መምጣቱን ነው የአፍሮባሮሜትር የዳሰሳ ጥናት ያሳየው።
ኢትዮጵያም በዳሰሳ ጥናቱ የተካተተች ሲሆን ለፖሊሶች ጉቦ በመክፈል ድጋፍ በማግኘት 22ኛ ደረጃን ይዛለች፤ አስተያየታቸውን ከሰጡ ኢትዮጵያውያን 35 በመቶው ለፖሊሶች ጉቦ ከፍለው ድጋፍ እንዳገኙ ገልጸዋል ይላል ጥናቱ።
ፖሊሶች የሙያ መርህን እና የዜጎችን መብት አክብሮ በመንቀሳቀስ ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያ ከ39ኙ በዳሰሳ ጥናቱ ከተካተቱ ሀገራት 13ኛ ደረጃን ይዛለች።
በአፍሪካ ፖሊሶች ሙያቸውን አክብረው ይሰራሉ ብለው የሚያምኑት 32 በመቶው ብቻ መሆናቸውን የጠቀሰው ጥናቱ፥ ወታደሮች በአንጻራዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ወደ ስልጣን የመጡ መሪዎችን በተኩባቸው ሀገራት ለፖሊሶች ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን አብራርቷል።
ቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር፣ ቤኒን እና ማሊ ፖሊሶች ሙያዊ ግዴታቸውን በሚገባ የማይወጡባቸውና የሰው ልጆችን መብቶች የማያከብሩባቸው ተብለው ከፊት ተቀምጠዋል።
ጉቦ የሚቀበሉ ፖሊሶች የተበራከቱባቸው 10 የአፍሪካ ሀገራትን ቀጥሎ ቀርበዋል፦
1. ላይቤሪያ
2. ናይጀሪያ
3. ሴራሊዮን
4. ኡጋንዳ
5. ኮንጎ ብራዛቪል
6. ካሜሮን
7. ቡርኪናፋሶ
8. ጊኒ
9. ኬንያ
10. ጋቦን