በ2023 የሀገራት የሙስና ደረጃ ኢትዮጵያ ስንተኛ ላይ ተቀምጣለች?
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የ180 ሀገራትን የሙስና ተጋላጭነት በማጥናት ደረጃቸውን ይፋ አድርጓል
ሶማሊያ በ2023ም ቀዳሚዋ ሙስና የተንሰራፋባት ሀገር መሆኗ ተመላክቷል
የፍትህ ስርአት መዳከም በመላው አለም ሙስና እንዲስፋፋ እያደረገ ይገኛል አለ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል።
ተቋሙ የ2023 የሀገራት የሙስና ደረጃን ይፋ አድርጓል።
23 ሀገራት በ2022 ከነበራቸው ደረጃ ዝቅ ብለዋል ያለው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት፥ ከ2016 ጀምሮ የህግ የበላይነት መከበርና ፍትህ የማስፈን ጥረት እየተዳከመ መሄዱን ጠቁሟል።
“የፍትህ ስርአቱ አጥፊዎችን ካልቀጣና የመንግስት አሰራርን ካልተቆጣጠረ ሙስና መንሰራፋቱ አይቀሬ ነው ብለዋል” የተቋሙ ሊቀመንበር ፍራንሲዮስ ቫለሪያን።
ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርአት የገነቡት እንደ አይስላንድ፣ ኔዘርላንድስ እና ስዊድን ያሉ ሀገራት በ2023 የሙስና ደረጃ የተሰጣቸው ነጥብ ዝቅ ብሏል።
በ2023 ደረጃቸውን ማሻሻል የቻሉት አየርላንድ፣ ደቡብ ኮሪያና ቬይትናምን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ብቻ ናቸው።
ዴንማርክ ከ100 ነጥብ 90 በማግኘት ለስድስተኛ ተከታታይ አመት ዝቅተኛ ወይንም ምንም ሙስና የማይታይባት ሀገር ሆናለች። ፊንላንድ እና ኒውዝላንድ ደግሞ በ87 እና 85 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ኖርዌይ፣ ሲንጋፖር፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጀርመን እና ሉግዘንበርግ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የ2023 ሪፖርት ያመላክታል።
ካለፈው አመት በአንድ ነጥብ ዝቅ ያለችው ኢትዮጵያም በ37 ነጥብ 98ኛ ደረጃን ይዛለች።
ሶማሊያ በ2023ም ሙስና የተንሰራፋባት ሀገር በመሆን በ11 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ (180ኛ) ይዛለች።
ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ቬንዙዌላ፣ የመን፣ እና ሰሜን ኮሪያም ሙስና የተንሰራፋባቸው ሀገራት ተብለው በደረጃው ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።