ዜጎቻቸው በከፍተኛ ድብርት የተጠቁባቸው የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ከድህነት፣ ስራ አጥነትና ዋጋ ግሽበት ጋር የተያያዙ ችግሮች ለከፍተኛ ድብርት የሚያጋልጧቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል
ዋይዝቮተር የተሰኘ የጥናት ተቋም ይፋ ባደረገው የሀገራት የድብርት ምጣኔ ደረጃ ኢትዮጵያ 133ኛ ላይ ተቀምጣለች
ከፍተኛ ድብርት በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል የአዕምሮ ጤና በሽታ ነው።
በህክምና ሊድን የሚችለው የድብርት ህመም ሳይደረስበት ለረጅም ጊዜ ከቆየም ከባድ ጉዳት ያስከትላል።
ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ በመቆየት በስዎች ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስም እንደ ስኳር ካሉ በሽታዎች መካከል መመደብ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።
የድብርት ህመም በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚከሰት የሚነገር ሲሆን፥ በድንገት የሚከሰት ከባድ ሀዘን፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም ከማህበረሰብ መገለል ድብርት ከሚያስከትሉ ጉዳዮች በቀዳሚነት ይነሳሉ።
ሴቶችም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለድብርት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የስራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎች ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ፈታኝ ጉዳዮችም ለድብርት በማጋለጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ነው አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር የዘገበው።
ዋይዝቮተር የተሰኘ የጥናት ተቋም ይፋ ባደረገው ጥናትም በአፍሪካ የሚከሰቱ የድብርት ህመሞች ከኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ የብድር ጫና እና የዋጋ ንረት ከትምህርትና ጤና ክብካቤ አቅርቦት ክፍተት ጋር ተዳምረው የሚሊየኖችን ህይወት መረበሻቸውንና በርካቶችን ለድብርት ማጋለጣቸውን ነው ጥናቱ የሚያሳየው።
በአህጉሪቱ ስለድብርት ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንና ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ የያዛቸው ልማዳዊ እሳቤዎች በድብርት የሚሰቃዩ ሰዎች ችግራቸውን ለመግለጽና መፍትሄ ለመፈለግ እንዲቸገሩ አድርጓል ይላል።
ዋይዝቮተር ባወጣው የአለማቀፍ የድብርት ምጣኔ ደረጃ ግሪክ፣ ስፔንና ፖርቹጋል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ሀገራቱ የገጠማቸው የኢኮኖሚ ቀውስም ዜጎቻቸው ለከፍተኛ ድብርት እንዲጋለጡ በማግረግ ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል ተብሏል።
ኢትዮጵያን 133ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው ተቋሙ በአፍሪካ ከፍተኛ ድብርት የሚታይባቸውን 10 ሀገራት እና አለማቀፍ ደረጃቸውን እንደሚከተለው ዘርዝሯል፦
1. ቱኒዚያ - 5ኛ
2. ሞሮኮ - 7ኛ
3. ጋቦን - 15ኛ
4. ሊቢያ - 23ኛ
5. ዲአር ኮንጎ - 32ኛ
6. ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ - 36ኛ
7. ኢኳቶሪያል ጊኒ - 40ኛ
8. ሞሪሺየስ - 41ኛ
9. ኡጋንዳ - 47ኛ
10. ደቡብ አፍሪካ - 48ኛ