የአዕምሮ ጤናን በድምጽ የሚመረምር ቴክኖሎጂ በሚቀጥለው ወር ሙከራ ሊጀምር ነው
ከ15 እስከ 45 ሰከንድ የድምጽ ናሙና በመውሰድ የስሜት መዋዠቅንና ጭንቀትን ይለካል
ቴክኖሎጂው 80 በመቶ ለልጆች የአዕምሮ ጤና እክል አስተዋጽኦ ላላቸው ጦርነት፣ ጥቃትና ግጭት በመሰሉ ቁስሎች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሰንቋል
በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና እክል ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ እንደሆነ ባለሞያዎች ይናገራሉ።
በተለይም ግጭቶችና ጦርነቶች በመስፋፋታቸው እንዲሁም የህክምና ማዕከላትና ባለሞያዎች አነስተኛ መሆናቸው ቀውስ እየሆነ እንደሆነ ይነሳል።
የአዕምሮ ጤና እክል ከሌሎች የጤና ችግሮች ባልተናነሰ በግለሰብ፣ በቤተሰብና በማህበረሰብ ላይ ከባድ ጫና እያደረሰ ነው የሚሉት ባለሞያዎች፤ የማህበረሰቡ የተዛነፈ ግንዛቤና በመንግስት ትኩረት መነፈግ ችግሩ እንዲሰፋ ማድረጉን ይጠቅሳሉ።
ለአዕምሮ ህመም ታዳጊዎችና ወጣቶች ተገላጭነታቸው ከፍ ያለ መሆኑ ደግሞ የመፍትሄ እርምጃዎችን አበክሮ ፈልጓል።
ቴክኖሎጂን እንደ መፍትሄ በመጠቀም በድምጽ ብቻ የአዕምሮ ጤና እክልን የሚለይ ሰው ሰራሽ ክህሎት (አርቴሪሻል ኢንተለጀንስ) በቅርቡ ሙከራ እንደሚያደርግ ተነግሯል።
ቴክኖሎጂው ከ15 እስከ 45 ሰከንድ የድምጽ ናሙና በመውሰድ የስሜት መዋዠቅንና ጭንቀትን የሚለካ ሲሆን፤ የህክምና ክትትል አማራጮችንም ያቀርባሉ።
የቴክኖሎጂው ፈጣሪ ቲኪው ኢንተለጀንሲ የተባለ ድርጅት የአዕምሮ ጤና እክልን አበክሮ ለመከታተልና እክሉ ሳይጎለብና ታማሚው ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያስከትል ለማከም ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቁሟል።
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ያሬድ አለሙ ቴክኖሎጂው አሉታዊ ስሜትን በመለየትና በመለካት ግብረ-መልስ እንደሚሰጥ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
“ሁላችንም እንጨነቃለን። ግን የተወሰነው ህዝብ ጭንቀትን አሸንፎ መሻገር ያቃተው አለ። እና እየተደመረ እየተደመረ [ይሄዳል]። አንዳንድ ጊዜ በልጅነት ነው የሚጀምረው፤ 16፣ 17 ዓመት ላይ። አንዳንድ ጊዜ 30፣ 35 ዓመት ላይ ይሆናል። ይሄድ ይሄድና ውስጥሽ እየተጎዳ ይመጣል። በሌላ እይታ ሰው በቀላሉ እየተጓዘ አንቺ 200 ኪሎ ተሸክመሽ እንደመሄድ ነው። የእነሱ በቀላሉ መጓዝና የአንቺ መጓዝ የተለያየ ነው። በባህል ምክንያተትም ለሰው ለመናገር አስቸጋሪ ይሆናል። ‘እያቃተኝ ነው፤ ራሴን ላጠፋ ነው’ ብሎ መናገር ይከብዳቸዋል። የእኛ አልጎሪዝም [ቀድሞ በተዘጋጀ ጽሁፍ} አንድ አንቀጽ ያነቡና ተንትኖ ወዲያው ግብረ-መልስ ይሰጣል” በማለት የቴክኖሎጂውን መፍትሄነት አብራርተዋል።
ቴክኖሎጂው እንደ ጤና እክሉ ስፋትና ደረጃም የቀረቡ የህክምና አማራጮች ምን ያህል ለውጥ አመጡ የሚለውም እንደሚመዘን ገልጸዋል።
ለአዕምሮ ጤና ቴክኖሎጂን እንደ መፍትሄ መጠቀሙ አነስተኛ የክህምና ማዕከላት ላላት ሀገር ሸክም እንደሚያቃልልም ዶ/ር ያሬድ ተናግረዋል። ልምድ በሌላቸው ባለሞያዎችና ከፍተኛ ምልክት በሚያሳዩ ታካሚዎች መሀል ያለውን ሰፊ ልዩነት ቴክኖሎጂው እንደሚያጠብም ገልጸዋል
“ክህምና የሚሰጥ የተወሰነ ባለሞያ ነው ያለው። ለዚህ የተወሰነ ባለሞያ ይህን መረጃ ከሰጠነው እንዴት አድርጎ እንደሚከታተል? ተሻለው አልተሻለውም? የሚለውን ታካሚውም ይጠቀማል፤ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ባለሞያዎችም ለውጥ ለማምጣት ያግዛል” ብለዋል።
የአዕምሮ ጤና የወጣቶች የዛሬ እክል፤ የጎልማሶች ደግሞ የነገ ችግር መሆኑን ያሰምራሉ። ለዚህም ቴክኖሎጂው ኢላማ ያደረገው ልጆችንና ወጣቶችን ነው ይላሉ።
የልጆች 80 በመቶው የአዕምሮ ጤና እክል ጦርነት፣ ጥቃትና ግጭት በመሰሉ ቁስሎች (ትራማ) የሚመጣ ነው የሚሉት ዶ/ር ያሬድ አለሙ፤ በኢትዮጵያ ይህን ለማከም በጣት የሚቆጠሩ ባለሞያዎች ብቻ እንዳሉ አንስተዋል። ይህን ክፍተት ቴክኖሎጃቸው እንደሚሞላ ተናግረዋል። በግጭት በተጠቁ ቦታዎች ላይም አገልግሎቱን በመስጠት የህክምና አማራጮችን ከማቅረብ ባለፈ በግጭት ጊዜ ባለሞያዎችን ለማሰልጠን እንደሚያግዝ ገልጸዋል። በዚህም በተለዩ 15 ቦታዎች ላይ መርሃ-ግብር እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የዚህ ቴክኖሎጂ ሙከራ በሚቀጥለው ወር በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይጀምራል ተብሏል። የቴክኖሎጂው ሙከራ እስኪረጋገጥ ድረስ የጤና ባለሞያዎች ብቻ የሚገለገሉበት ሲሆን፤ ሙከራው ውጤታማ ሲሆን ሁሉም ሰው እንዲያገኘው ክፍት እንደሚሆን ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
“ድረ ገጽ በማይኩ የሆነ ነገር ተናገሪ ይልሻል፤ ወደ ስፒከሩ ጠጋ ብለሽ ታነቢያለሽ። ከዚያ [በመለካት] ግብረ-መልስ ይሰጣል ማለት ነው። ምልክቱ ከፍተኛ ከሆነ ለመታከም የሚፈልገው ሰው ምን አይነት አቅም አለው? የሚለውን በመለየት ያቀርባል” ብለዋል።
ህጻናትና ወጣቶች ጤናማ አስተዳደግ እንዲኖራቸው የእክሉን ስረ-መሰረት በመለየት ተገቢውን ህክምና መስጠት ድርጅቱ ምሰሶ መሆኑነን ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።