በርካታ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑባቸው የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸው
11.1 ሚሊየን ህጻናት ከትምህርት የራቁባት ኢትዮጵያ በደረጃው ሁለተኛ ላይ ትገኛለች
ጦርነት ፣ ግጭት ፣ ድህነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ህጻናቱን ከትምህርት ገበታቸው ያፈናቀሉ ዋነኛ ምክንያት ናቸው
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) መረጃ መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ ከ6 እስከ 18 አመት እድሜ ላይ የሚገኙ 244 ሚሊየን ህጻናት እና ወጣቶች ከትምህርት ውጪ ናቸው፡፡
እስካለፈው ሰኔ ድረስ ደግሞ በአፍሪካ 24 ሀገራት ብቻ ከ14300 የሚልቁ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡
በርካታ ትምህርት ቤቶች ከተዘጉባቸው ሀገራት መካከል ቡርኪናፋሶ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ናይጄሪያ እና ኒጀር ተጠቃሽ ናቸው።
ከግጭቶች፣ ከተሳሳቱ የመንግስት ፖሊሲዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ ጎን ለጎን ድህነት ለትምህርት ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የዘለቀ ችግር ነው፡፡
ዝቅተኛ ኢኮኖሚ በሚገኙባቸው ሀገራት ጦርነት እና ግጭት እንኳን ባይኖር በኢኮኖሚ ሁኔታ የተነሳ ህጻናት ወደ ትምህርት ከሚላኩ ይልቅ ወደ ስራ የሚሰማሩበት አጋጣሚ ከፍ ይላል፡፡
በትምህርት ተደራሽነት ላይ ያለው አስገራሚ ልዩነት በቅርብ ጊዜ በተደረገ ጥናት የተረጋገጠ ሲሆን ፤ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ውስጥ ለትምህርት ከደረሱ ሕፃናትና ወጣቶች መካከል 33 በመቶ የመማር ዕድል ተነፍጓቸዋል፡፡
በሰላም ዕጦት ከሚዘጉ ትምህርት ቤቶች ባለፈም በበጀት እጥረት ስራ የሚያቆሙት ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ የሚጠቅሰው የዩኒስኮ ሪፖርት፤ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት በ2022 በአማካይ ለአንድ ተማሪ 55 ዶላር ብቻ ሲመድቡ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ደግሞ እስከ 8543 ዶላር ድረስ ያወጣሉ ብሏል፡፡
ሪፖርቱ በርካታ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑባቸው የአፍሪካ ሀገራትን ደረጃ ባወጣበት 18.18 ሚሊየን ህጻናት ከትምህርት ውጪ የሆኑባትን ናይጄርያ ቀዳሚ አድርጓታል፡፡
11.1 ሚሊየን ህጻናት ከትምህርት የተቆራረጡባት ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ደረጃ ስትይዝ ታንዛኒያ ፣ ዲ አር ኮንጎ እና ሱዳን ይከተላሉ፡፡