በ2025 ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የታየባቸው የአፍሪካ ሀገራት
ዜጎች ለምግብ፣ መጠለያ፣ ትራንስፖርት፣ ጤና እና ሌሎችም መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚጠየቁት ወጪ መናር ፈታኝ ሆኗል
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
የኑሮ ዋጋ መናር ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማሟላት አቅማቸው፣ የመቆጠብ፣ ንግዶችን ማቋቋም እና አስፈላጊ ሸቀጦችን ለመግዛት ያላቸውን አቅም የሚገድብ ነው፡፡
ከፍተኛ የኑሮ ንረት ባለባቸው ሀገሮች የመደበኛ ኑሮ ወጪዎችን ለመሸፈን መቸገር እንዲሁም ይህ የገቢ እና የኑሮ ዋጋ አለመጣጠን የኑሮ ደረጃን የሚቀንስ፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን የሚጎዳ እንዲሁም ድህነትን ሊያባብስ የሚችል መሆኑ ይነገራል፡፡
እንደ መኖሪያ ቤት፣ ምግብ፣ ትራንስፖርት ፣ የጤና እንክብካቤ እና ትምህርት ያሉ መሰረታዊ ፍላጎቶች እና አገልግሎቶች ዋጋ ተመጣጣኝነት ለኑሮ ውድነት መለኪያነት ያገለግላሉ፡፡
በመሰረታዊ ሸቀጥ እና አገልግሎቶች እየጨመረ የሚገኘው ዋጋ ከሚያባብሰው ድህነት ባለፈ ማህበራዊ ቀውስ እና ወንጀልን ሊያባበስ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
በብዙ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች እያደገ ከሚሄደው ወጪ ጋር ተላምደው ሲቀጥሉ፤ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ደግሞ የችግሩን ጫና ይጋፈጣሉ።
ትናንሽ እና መካከለኛ ንግዶች የአገልግሎት፣ የኪራይ እና የደመወዝ ሂሳቦቻቸው እየጨመረ መሄድ የሥራ ማስኬጃ ወጪያቸው እንዲያድግ ያደርጋል፡፡
ለአፍሪካ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑት ጥቃቅን እና መካከለኛ ኩባንያዎች በመሰል ተግዳሮቶች መፈተናቸው ከስራ እንዲወጡ ሊያስገድዳቸው እንደሚችልም ስጋትን ፈጥሯል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በ2025 መጀመሪያ በአፍሪካ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ያስመዘገቡ ሀገራትን ዝርዝር ባወጣበት መረጃው ኢትዮጵያን ቀዳሚ አድርጓታል፡፡
በባለፈው አመት መለኪያ አራተኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ በዚህ አመት ወደ አንደኛ ደረጃ ከፍ ያለችው ሞዛምቢክ ፣ ሴኔጋል እና አይቮሪኮስት በዚህኛው አመት መጠነኛ ማሻሻያዎችን አስመዝግበዋል፡፡
በ2025 መጀመሪያ በኑሮ ውድነት ቦትስዋና ፣ ሞዛምቢክ እና አይቪሪኮስት ኢትዮጵን በመከተል ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡