በ2025 መጀመሪያ ወርሀዊ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያላቸው ማህበራዊ ገጾች
በ2024 መጨረሻ በአለም አቀፍ ደረጃ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚ 5.22 ቢሊየን ደርሷል
በተጠናቀው የፈረንጆቹ አመት 12 ወራት 256 ሚሊየን አዳዲስ ተጠቃሚዎች ማህበራዊ ትስስር ገጾች ተቀላቅለዋል ተብሏል
አለምን በማቀራረብ ትልቅ ውለታ ውለዋል የሚባሉት የማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጠቃሚዎቻቸው ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየተመነደገ ይገኛል፡፡
በዋናነት መረጃዎችን ለማግኝት ፣ መልዕክቶችን ለመለዋወጥ ፣ ለመዘናኛ ፣ ለፋይናንስ እንቅስቃሴ ፣ ለግብይት እና ሌሎችም ፉይዳዎች ላይ አገልግሎት የሚሰጡት ገጾቹ፤ እንደ ቦታው እና ሁኔታው የተጠቃሚዎቻቸው አይነት እና ብዛት ይለያያል፡፡
የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ቁጥር በአመት በ5.2 በመቶ እድገት ሲያስመዘግብ፤ በእያንዳንዱ ሰከንድ ውስጥ ደግሞ 8.1 አዳዲስ ተጠቃሚዎች እንደሚቀላቀሉ የግሎባል ዲጂታል ኦቨር ቪው መረጃ ያመላክታል፡፡
2024 መጨረሻ ላይ በዓለም ዙሪያ 5.22 ቢሊየን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሲኖሩ ይህም ከጠቅላላው የአለም ህዝብ 63.8 በመቶው ጋር እኩል ነው።
ባለፉት 12 ወራት ውስጥ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደጉን ሲቀጥል፤ በአመቱ 256 ሚሊዮን አዲስ ተጠቃሚዎች ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ተቀላቅለዋል፡፡
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት 94.5 በመቶ የሚሆኑ የአለም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በየወሩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ይጠቀማሉ፡፡
ቋሚ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሚባሉ ሰዎች በአማካኝ 6.8 በመቶ የተለያዩ መተግበሪያዎችን እንደሚጎበኙ መረጃው ጠቁሟል፡፡
ይህ ማለት በቀን ውስጥ 2ሰዓት ከ19 ደቂቃ በገጾቹ ላይ የሚያጠፉ ሲሆን አንድ ላይ ሲደመር ዓለም በየቀኑ ከ12 ቢሊዮን ሰአታት በላይ ማህበራዊ ገጽ ላይ ያጠፋል እንደማለት ነው፡፡
በ2025 መጀመሪያ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ካሏቸው ማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል የሜታ ኩባንያ አካል የሆነው ፌስቡክ ከ 3 ቢሊየን በላይ ወርሀዊ ተጠቃሚዎችን በመያዝ በአለም ላይ ቀዳሚው ነው፡፡
ዩትዩብ 2.530 ቢሊየን ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ 2 ቢሊየን ቲክቶክ ደግሞ 1.6 ቢሊየን ተጠቃሚዎችን በመያዝ በደረጃ ተቀምጠዋል፡፡
የሜታ ኩባንያ ኢንስታግራም ፣ ዋትስአፕ እና ፌስቡክ የተባሉ ማህበራዊ ሚድያዎችን ከ1-5 ባለው ደረጃ ውስጥ በማካተት ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር ችሏል፡፡