በ2024 በርካታ ተጓዦችን ያስተናገዱ የአፍሪካ አውሮፕላን ማረፊያዎች የትኞቹ ናቸው?
በአህጉሪቱ በርካታ ደንበኞችን በማስተናገድ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል
ዓመቱ የአቭየሽን ዘረፍ በርካታ ተግዳሮቶችን ቢያስተናግድም ከፍተኛ እድገት ያስመዘገበበት ነበር
የአቭየሽን ኢንዱስትሪ ለስራ፣ ለንግድ፣ ለጉብኝት እና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚጓዙ መንገደኞችን በመላው አለም በማገናኝት በፍጥነት እያደገ ይገኛል፡፡
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞች ለስራ ወይም ለእረፍት በሚያደርጉት ጉዞ አውሮፕላኖችን ይጠቀማሉ ከዚህ ባለፈም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጭነቶች ሰማያትን አቋርጠው ወደ መደረሻቸው ያመራሉ።
የተለያዩ የአውሮፕላን አደጋዎች ፣ የህግ ቁጥጥሮች ፣ እና ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታዎች የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፤ በአለም አቀፍ ደረጃ 2024 ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ወሳኝ አመት እንደነበር የግሎባል ኤርላይን ስኬጁል ዳታ መረጃ አመላክቷል፡፡
የዓለማችን ስራ የሚበዛባቸው እና በርካታ ደንበኞችን የሚያስተናግዱ አውሮፕላን ማረፊያዎች በአጠቃላይ ከ411 ሚሊዮን በላይ ተሳፋሪዎችን አስተናግደዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ዱባይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (ዲኤክስቢ) በአመቱ 60.2 ሚሊዮን ተጓዦችን በማስተናገድ የዓለማችን ስራ የሚበዛበት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደረጃን በቀዳሚነት አስጠብቋል፡፡
የለንደን ሄትሮው አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ48.4 ሚሊየን ተጓዦች የዱባይ አየር መንገድን በቅርበት ይከተላል ይህም ቀደም ብሎ ከነበረው ዓመት የ4 በመቶ እድገት የታየበት ነው፡፡
በአፍሪካ የከተሞች መስፋፋት ፣ የንግድ ግንኙነት ማደግ እና ቱሪዝም በአህጉሩ የአየር ትራንስፖር ዘርፍ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
1.ካይሮ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ
በአህጉሪቷ በደንበኞች ከሚጨናነቁ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል ከ18 ሚሊየን በላይ ተጓዦችን የሚያስተናግደው የካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ቀዳሚ ሆኗል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው ከፈረንጆቹ 2019 አንጻር የ46 በመቶ አፈጻጸም ብላጫ ሲያስመዘግብ በአንጻሩ ከ2023 አኳያ ደግሞ የ11 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
ከእስያ፣ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከሰሜን አሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ሲያሳድግ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናም ተመራጭ ከሆኑ የአውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
2.የጆሃንስበርግ ኦ.አር ታምቦ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ
የደቡብ አፍሪካው የጆሃንስበርግ ኦ.አር አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሌላው የአፍሪካ አቪዬሽን ቁልፍ ሚና ተጫዋች ተቋም ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2024 ከ12 ሚሊየን 272 ሺህ በላይ መንገደኞችን ያስተናገደው አውሮፕላን ማረፊያው ከ2019 ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ ቅናሽ ቢያሳይም ከ2023 አንጻር ግን 4 በመቶ እድገት አሳይቷል።
3.አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ
በአፍሪካ ምርጥ ከሚባሉ አውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ2024 ከ12 ሚሊየን 99 ሺህ በላይ ተጓዦች ነበሩት፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው በ2019 ከነበረው አፈጻጸም በ32 በመቶ ብልጫ አስመዝግቧል፡፡
ቀጣይነት ያለው እድገት እያሳየ እንደሚገኝ የተነገረለት አውሮፕላን ማረፊያው፤ በተጠናቀቀው አመት የነበረው እድገት ከ2023 ጋር ሲነፃፀር 11 በመቶ እድገት የታየበት ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አህጉር እና በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን መዳረሻዎች እያሰፋ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡