ዝሆኑቹ በሰማቸው ሲጠሩ ኩምቢያቸውን እና ጆሯችውን በማንቀሳቀስ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሏል
በአፍሪካ የሚገኙ ዝሆኖች በስም እየተጠራሩ እንደሚግባቡ አዲስ የጥናት ውጤት አመላክቷል፡፡
በኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርስቲ የስነ- ምህዳር ተመራማሪዎች ይፋ የተደረገው አዲስ ግኝት ዝሆኖቹ በአስገራሚ ሁኔታ በተለያየ ስያሜ እንደሚጠራሩ እና ለጥሪው የሚሰጡት ምላሽም አንዱ ከሌላው የተለየ ስም እንዳለው አመላካች መሆኑን ነው የጠቆመው።
ተመራማሪዎቹ ዝሆኖቹ የሚግባቡበትን መንገድ ለማጥናት ባደረጉት ክትትል ለሰዎች መስማት አዳጋች በሆነ ድምጽ መልዕክት ሲለዋወጡ እና ለዚህም ምላሽ ሲሰጡ ማስተዋላቸውን አመላክተዋል፡፡
ዝሆኑቹ ለእነርሱ በተሰጠ ስያሜ ሲጠሩ ኩምቢያቸውን እና ጆሯችውን በማንቀሳቀስ ምላሽ የሚሰጡ ሲሆን ቀጥሎም ወደ ጠራቸው ዝሆን በመቅረብ እንደሚግባቡ ነው አጥኚዎቹ የገለጹት፡፡
ዝሆኖቹ ለጥሪ የሚጠቀሙት ድምጽ ስም መሆኑን ለማረጋገጥ የተለያዩ የድምጽ መመርመሪያ ማሽኖችን ሳይንቲስቶቹ ጥቅም ላይ ያዋሉ ሲሆን ማሽኖቹ 28 በመቶ የሚሆነውን ጊዜ የትኛው ስያሜ ለየትኛው ዝሆን የተሰጠ መሆኑን በትክክል ገምተዋል ነው የተባለው፡፡
በኬንያ አምቦሲሊ ፓርክ በተደረገው ጥናት ዝሆኖች እንደሰው ልጅ ስሞችን እንደሚጠቀሙ ብናረጋግጥም ሁሉም ዝሆኖች በስያሜ ይግባባሉ የሚለው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልገናል ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡
ከዚህ ቀደም የወጡ ጥናቶች ዝሆኖች ጠንካራ የመግባብያ ስርአት ያላቸው እንስሳር መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይህ አዲስ ግኝት ደግሞ ዝሆኖች ማህበራዊ ተግባቦት ያላቸው ፍጡሮች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል፡፡
በቀቀን (ፓሮት)እና ዶልፊኖች የመግባብያ ስያሜዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ በሚል የስነ-ምህዳር ተመራማሪዎች ተመሳሳይ ምርምሮችን እያደረጉ ይገኛሉ።