በሴንት አንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት፥ የጦጣዎች እና የሰው ልጆች ምልክት ቋንቋዎች ከ95 በመቶ በላይ ተመሳሳይነት እንዳላቸው አሳይቷል
የሰው ልጆች እና ጦጣዎች ተመሳሳይ የምልክት ቋንቋ ይጠቀማሉ - ጥናት
የሰው ልጅ አፈጣጠርን በተመለከተ ሁለት አይነት እሳቤዎችን የሚያራምዱ ተመራማሪዎች አሉ።
የሰው ልጅ በአንድ አምላክ የተፈጠረ ነው የሚሉት (ክሬሽኒስት) በአንድ ጎራ ተሰልፏል።
የሰው ልጅ አሁን ያለውን መልክና ቁመና ከመያዙ በፊት ዝግመታዊ ሂደቶችን አልፏል የሚሉት (ኢቮሊሽስትኒት) እሳቤ አቀንቃኞች ደግሞ በሌላኛው ወገን ሆነው ይሞግታሉ።
የሰው ልጅ በዝግመታዊ ሂደት ያለፈ ነው የሚሉት ተመራማሪዎች በተለያየ ጊዜ ይፋ የሚያደርጓቸው ምርምሮች የሰው ልጅ ከቀደምቶቹ አምሳያዎቹ በርካታ ባህሪያትን መውረሱን ያሳያሉ።
ሰዎች ቀረብ ከሚሏቸው እንደ ጦጣ እና ዝንጀሮ ካሉት ከ90 በመቶ በላይ ባህሪያትን እንደሚጋሩም ነው የሚያነሱት።
በሴንት አንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ጥናትም የሰው ልጅ ከጦጣዎች ጋር ተመሳሳይ የምልክት ቋንቋዎችን እንደሚጠቀም ተደርሶበታል ይላል።
የጦጣዎችን እንቅስቃሴ እና ተግባቦት በቪዲዮ በመቅረጽና በጎፈቃደኛ ሰዎች ትርጉም እንዲሰጡት በማድረግ የተካሄደው ጥናት ይህንኑ ማረጋገጡ ነው የተገለጸው።
ጦጣዎችም ሆኑ መሰል ፍጥረቶች የሚጠቀሟቸው የምልክት ቋንቋዎች የሰው ልጆች አሁንም ድረስ ከሚጠቀሟቸው የምልክት ቋንቋዎች እና በሰውነት አካላት መልዕክት መለዋወጫ መንገዶች ተመሳሳይነት እንዳለው ተደርሶበታል ይላል ጥናቱ።
ጥናቱን በበላይነት የመሩት ዶክተር ክርስቲ ግርሃም እንደሚሉት፥ የጦጣዎች እና የሰው ልጆች ምልክት ቋንቋዎች ከ95 በመቶ በላይ ተመሳሳይነት አላቸው።
ይህም የንግግር ቋንቋ ከመጀመሩ በፊት የምልክት ቋንቋ ዋነኛው መግባቢያ እንደነበር ማሳያ አድርገው አቅርበውታል።
ለአመታት በተካሄዱ መሰል ጥናቶችም ዝንጀሮዎች ከ80 በላይ የምልክት ቋንቋዎችን እንደሚጠቀሙ ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ዶክተር ክርስቲ ይናገራሉ።
የፊታቸውን ገጽታ በመቀያየርና እጃቸን በመጠቀም “እንሂድ”፣ “እንብላ”፣ “ያን ምግብ ስጠኝ” የሚሉና መሰል ጥያቄና ትዕዛዞችን እንደሚከውኑ ነው ጥናቶቹ ያሳዩት።
በሴንት አንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሰበሰቡ የቪዲዮ ምስሎችንም በጎፈቃደኛ ሰዎች ተመልክተው ትርጉም እንዲሰጧቸው ተደርጓል።
በጎፈቃደኞቹ ለተቀመጡላቸው አማራጭ ትርጉሞች የሰጧቸው ፈጣን ምላሾችም ተመሳሳይ ሆነው ተገኝተዋል።
“ይህም የሰው ልጆች የሚጠቀሟቸው የምልክት ቋንቋዎች ከጦጣዎች ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ያመላክታል” ነው ያሉት ዶክተር ካትሪን ሆባይተር የተባሉ የጥናቱ ተሳታፊ።
ከዚህ ቀደም በጦጣ እና ዝንጀሮዎች የምልክት ቋንቋዎች ላይ ከተደረጉና ከተበየኑ ትርጓሜዎች ጋር ተመሳሳይ ሆኖ መገኘቱም ግርምትን የሚያጭር ነው ብለውታል።
በሰው ልጅ አመጣት ዙሪያ በሁለት ጎራ የተከፈሉ ተመራማሪዎች ሙግት ግን አሁንም ድረስ ቀጥሏል።