ሳኡዲዎች ከግመሎች ጋር የሚግባቡበት “ልዩ ቋንቋ” በአለም ቅርስነት ተመዝግቧል
አልሄዳ እየተባለ የሚጠራው ልዩ ቋንቋ ከ200 አመት በላይ እድሜ እንዳለው ተገልጿል
የሰለጠኑት “የበርሃ መርከቦች” ስማቸውንና የሚስጣቸውን ትዕዛዝ በአግባቡ መለየት ይችላሉ ተብሏል
የሳኡዲ አረቢያ ግመል አርቢዎች "ከበርሃ መርከቦቹ" ጋር የሚግባቡበትን “ልዩ ቋንቋ” ፈጥረዋል።
“አልሄዳ” እየተባለ የሚጠራው ልዩ ቋንቋ ባለፈው ወር በመንግስታቱ ድርጅት የሳይንስ እና ባህል ተቋም ዩኔስኮ በአለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
የሰለጠኑት ግመሎች(የቀረሃ መርከቦች) የባለቤቶቻቸውን ትዕዛዝ በፍጥነት ይቀበላሉ።
በአንድ ላይ እንዲያርፉም ሆነ ማዕበል ሲመጣ አቅጣጫ እንዲቀይሩና በጥንቃቄ እንዲንቀሳቀሱ አሳዳጊዎቻቸው የሚሰጧቸውን መመሪያም ለመተግበር አይቸገሩም።
በበርሃ ለረጅም ስአት ያለውሃ ጥም የሚጓዙት ግመሎች በሳኡዲ አረቢያ፣ የአረብ ኢምሬትስ እና ኦማን ሁነኛ የትራንስፖርት አማራጭ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።
ይህም ግመሎች ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች በስፋት እንዲካሄዱ እና የግመል ማርባት ስራም በስፋት እንዲካሄድ አድርጓል።
ሳኡዲዎች ከትውልድ ትውልድ ያስተላለፉት ግመሎችን የሚያነጋግሩበት ቋንቋም በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሲጠየቅ ቆይተዋል።
ሳኡዲ፣ ኤምሬትስ እና ኦማን በጋራ ያደረጉት ጥረትም ባለፈው ወር በመንግስታቱ ድርጅት የሳይንስ እና ባህል ተቋም ዩኔስኮ ምላሽ አግኝቶ “አልሄዳ” በአለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
ልዩ ቋንቋው ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውል ሲሆን፥ እያንዳንዱ ግመሎች በአሳዳጊዎቻቸው የተሰጣቸውን ስም ይለያሉ ተብሏል።
“ግመሎቹ የአሳዳጊዎቻቸውን ድምጽ ለይተው ምላሽ ይሰጣሉ፤ ሌሎች ሰዎች ሲጠሯቸው ግን አይሰሙም” ይላሉ ሃማድ አል ማሪ የተባሉ ከ100 በላይ ግመሎች ያሏቸው ግለሰብ።
የተራራቁ ግመሎችን በአንድ መንጋ እንዲጓዙ በማድረግ ከአውሎ ንፋስ ለመጠበቅም ይሄው ቋንቋ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ነው የሚናገሩት።
አሰልጣኞቹ ግመሎቹ ቀኝ እና ግራን እንዲለዩ፣ አፋቸውን እንዲከፍቱ እና ሸብረክ ብለው እንዲያርፉ እንደሚያለማምዱም መንሱር አል ቁቱላ የተሰኙት የአልሄዳ ቋንቋ አሰልጣኝ ይገልጻሉ።
ይህን እውቀትም ከአያትና አባታቸው መቅሰማቸውን ነው ለቲ አር ቲ ወርልድ የተናገሩት።
ከ200 አመት በላይ እድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት “አልሄዳ” በዩኔስኮ መመዝገቡ ቋንቋው እንዲጠበቅና እንዲስፋፋ ያግዛል ተብሏል።