በኢትዮጵያ የዝሆኖች ህልውና በከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቁ ባለስልጣኑ አስታወቀ
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የዝሆኖች ቁጥር ከ2ሺ አይልቅም ብለዋል
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የዝሆኖች ቁጥር ከ2ሺ አይልቅም ብለዋል
የዝሆኖች ህልውና በከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቁ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት የህግ ማስከበር ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጳውሎስ ለአል-ዐይን ኒውስ እንደተናገሩት ከሆነ በተለያዩ ፓርኮች ያለው የዝሆኖች ቁጥር እጅጉን እየቀነሰ መምጣቱን ተናግሯል፡፡
ለቁጥሩ መቀነስ የተደራጁና ህገወጥ አዳኞች ለህገ-ወጥ ንግድ (የዝሆን ጥርስ ለመሸጥ) በሚል ዝሆኖችን እየገደሉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
“ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የኦሞ፣ ባቢለ እና ማጎ ፓርኮች የነበሩ 19 ዝሆኖች ተገድሏል” ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
አሁን ላይ በፓርኮች የሚስተዋሉ ዝሆንን የመግደል ህገ-ወጥ ድርጊቶቹ እየተባባሱ በመምጣታቸው የዝሆን ህልውና እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ወድቋል ያሉት ዋና ዳሬክተሩ፤ አሁን ያለው ዝሆኖች ቁጥር ከ2ሺ እንደማይበልጥ አስታውቋል፡፡
ፓርክ በሚጠብቁ አካላት አማካኝነት አጥፊዎች (ተደራጅተው ህገ-ወጥ አደንን የሚፈጽሙ ሰዎችን) ወደ ህግ ለማቅረብ ጥረት ሲያደርግ የነበረ ቢሆነም አስካሁን የተወሰደው እርምጃ አስተማሪ አለመሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ዳሬክተሩ እንዳሉት በቀጣይ ዝሆኖችን ከመጥፋት ለመታደግ መንግስት በተለይም የፍትህ አካላት በህገወጥ የዝሆን አደን የተሰማሩ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
ከሁለት አመት በፊት በአንድ ሳምንት ውስጥ በደቡብ ክልል በሚገኘው ማጎ ብሄራዊ ፓርክ ስምንት ዝሆኖች መገደላቸውን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ የፓርኩ ዋርደንም ከተገደሉረት ስምንት ዝሆኖች ውስጥ የስድስቱ ዝሆኖች ጥርስ መወሰዱን ገልጾ ነበር፡፡በ2007 ዓ.ም በተደረገ ቆጠራ በማጎ ብሄራዊ ፓርክ 170 የሆኑ ዝሆኖች ነበሩ፡፡