አፍሪካ ምን ማድረግ እንዳለባት ማንም ሊያዛት እንደማይገባ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ተናገሩ
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የሚወዳጁ የአፍሪካ ሀገራትን እንዳትቀጣም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር በዋሸንግተን ተወያይተዋል
አፍሪካ ምን ማድረግ እንዳለባት ማንም ሊያዛት እንደማይገባ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሰባተኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን ጦርነቱን ተከትሎ ምዕራባዊያን ሩሲያን ከተቀረው ዓለም ለመነጠል የተለያዩ ጫናዎችን እያደረጉ ያገኛሉ።
አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባዊያን ሀገራት ዩክሬን በሩሲያ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከመስጡ ጎን ለጎን በሞስኮ ላይ ማዕቀብ በመጣል ላይ ናቸው።
ይህ በዚህ እንዳለም አፍሪካን ጨምሮ ከሩሲያ ጋር ወዳጅነትን በሚመሰርቱ ሀገራት ላይ ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ ላይ ናቸው።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ወደ ዋሸንግተን ተጉዘው በነጩ ቤተ መንግስት ከአሜሪካ አቻቸው ጋር ተወያይተዋል።
ሩሲያ የየትኛውም የዓለማችን ባለጸጋ ሀገር ጋር የተለየ ግንኙነት የላትም ያሉት ፕሬዝዳንት ራማፎዛ አሜሪካም በአፍሪካ የተለየ ተጽዕኖ ማድረግ እንደሌለባት አክለዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ተጽዕኖ ልታደርግ እንደማይገባ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ አፍሪካ ምን ማድረግ እንደሚገባት ማንም መናገር አይችልም ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካ አፍሪካ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ የተለያዩ ጫናዎችን እያደረገች ሲሆን በአንድ ወር ውስጥ በተመድ የዋሸንግተን ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ እና የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ አፍሪካ በመምጣት ስድስት ሀገራትን ጎብኝተው መመለሳቸው ይታወሳል።
የመሪዎቹ ወደ አፍሪካ መምጣት ዋና አላማው ከሩሲያ ጋር ጠያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ጫና መፍጠር ሲሆን አፍሪካ ከሩሲያ ከአፈር ማዳበሪያ እና ስንዴ ውጪ ሌሎች ምርቶችን መግዛት እንደማይችሉ ተናግረውም ነበር።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በምዕራብ አፍሪካ ባደረጉት ጉብኝት አፍሪካ በሩሲያ ላይ የተለሳለሰ አቋም አሳይተዋል በሚልም ትችት ሰንዝረዋል።