አሜሪካዊቷ ከፍተኛ ዲፕሎማት፤ የአፍሪካ ሃገራት “ሊያልፉት የማይገባ ቀይ መስመር አለ” ማለታቸው እያነጋገረ ነው
ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፤ የአፍሪካ ሃገራት ከስንዴ እና ማዳበሪያ ውጭ ከሩሲያ ምንም ነገር እንዳይገዙ አስጠንቅቀዋል
አምባሳደር ሊንዳ ከሰሞኑ ሶስት የአፍሪካ ሃገራትን መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው
አፍሮ አሜሪካዊቷ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት፤ የአፍሪካ ሃገራት ከስንዴ እና ማዳበሪያ ውጭ ከሩሲያ ምንም ነገር እንዳይገዙ ማስጠንቀቃቸው እያነጋገረ ነው፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የአፍሪካ ሃገራት ሊያልፉት የማይገባ ቀይ መስመር እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ግሪንፊልድ ከሰሞኑ ኡጋንዳን፣ ጋናን እና ኬፕቨርዴን ጎብኝተዋል፡፡ ጉብኝታቸው የሩሲያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰርጌ ላቭሮቭን የአፍሪካ ጉብኝት ተከትሎ የተደረገ ነው፡፡ ዲፕሎማቷ ግን ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ለመፎካከር በሚል ወደ አፍሪካ እንዳልመጡ ተናግረዋል፡፡
በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ለተዳረገችው አፍሪካ መፍትሔ ለማፈላለግ በማሰብ እንደሚጎበኟትም ነበር ከጉዞው በፊት የተናገሩት፡፡
ሆኖም ኡጋንዳ ከደረሱ በኋላ የአፍሪካ ሃገራት ሊያልፉት የማይገባ ቀይ መስመር እንዳለ መናገራቸው እያነጋገረ ነው፡፡
“የአፍሪካ ሃገራት እህልን ጨምሮ የሩሲያን የግብርና ምርቶች እና የአፈር ማዳበሪያን ሊገዙ ይችላሉ” ሲሉ ለአሶሼትድ ፕሬስ የተናገሩት አምባሳደር ሊንዳ ነገር ግን ነዳጅንና የነዳጅ ምርቶችን ሊገበያዩ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
የሚገበያዩ ከሆነ በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን መጣስ እንደሚሆን ነው አምባሳደሯ የተናገሩት፡፡ በመሆኑም “ማዕቀቡን እንዳይጥሱ እናሳስባለን” ብለዋል ይህ ካልሆነ ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ሊጠብቃቸው እንደሚችል በማስጠንቀቅ፡፡
ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገራት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ገለልተኛ አቋምን መርጠዋል፡፡ ሩሲያን አውግዘው ከምዕራባውያን ጎን እንዲሰለፉ ቢፈለግም ከኬንያ በስተቀር አቋማቸውን በአደባባይ ለማንጸባረቅ የደፈሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ይህ የጦርነቱን ዳፋ ከመቅመስ አላዳናቸውም፡፡ በተለይም ብዙዎቹ በሩሲያ እና ዩክሬን የስንዴና ሌሎች የግብርና ምርቶች እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ መሆናቸው ለከፋ ጉዳት ዳርጓቸዋል፡፡ ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር እና ኑሮ ውድነት የተዳረጉም ጥቂት አይደሉም፡፡
በዚህ መካከል ነው የአፍሮ አሜሪካዊቷ የአምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ማስጠንቀቂያ የመጣው፡፡ ምን ያህል ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል አልታወቀም፡፡ ነዳጅን ጨምሮ በከፋ የሸቀጦች ዋጋ ንረት እየተጠበሱ መሆኑን ተከትሎ የመጣውን እንቀበላለን በሚል የሩሲያን ነዳጅ ሊገዙ የሚችሉ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡
ከአምባሳደር ሊንዳ ጉብኝት በፊት “ምን ማድረግ እንዳለብን ማንም ሊነግረን አይችልም” በሚል የተናገሩት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ከጉብኝቱ በኋላ “አፍሪካን ከአንጀት መርዳት ከፈለጉ ባልተሳተፍንበት ጦርነት ከጣሉት ማዕቀብ ሊለዩን ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡