የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፤ “አፍሪካ ምን መምረጥ እንዳለባት አሜሪካ አታዝም” አሉ
አንቶኒ ብሊንከን፤ “የሩሲያው ዋግነር ቡድን ባለመረጋጋት ውስጥ ሃብትን የሚዝቅና በደል የሚፈጽም ቡድን ነው” ሲሉ ከሰዋል
“በአፍሪካ ለታየው ዋጋ ንረት ምክንያት ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ነው” የሚለውን ክስ ብሊንከን ውድቅ አደረጉ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ አፍሪካ ምን መምረጥ እንዳለባት አሜሪካ “አታዝም” አሉ።
ሩሲያን ከዓለም ለመነጠል ያለመ በተባለው የአፍሪካ ጉብኝት ላይ የሚገኙት አንቶኒ ብሊንከን፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ይበጃል ያሉትን አዲስ የስትራቴጂ ሰነድ አቅርበዋል።
ብሊንከን ባቀረቡት ጽሁፍ፡ የአፍሪካ ሀገራት ለገዛ እድገታቸው የሚታገሉ ሳይሆን የሌሎች መሳሪያ እንደሆኑ ተደረገው ሲታዩ መቆየታቸውም አንስተዋል።
"የአፍሪካ ሀገራት ከህዝቦቻቸው ፍላጎት ውጭ በሆነ መልኩ፤ የዓለም ኃያላን ፉከክር በሚያደርጉበት ጉዳይ ላይ አቋም እንዲይዙ ሲነገራቸው ነበር" ነው ያሉት ብሊንከን።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ብሊንከን፤ ሀገራቸው አሜሪካ መሰል ጫና እንደማትደገፍ የገለጹ ሲሆን፤ አሜሪካ አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ቅድሚያ ሰጥታ የምትሰራባቸው ጉዳዮች ቢኖሩ “ዴሞክራሲ፣ ሰላም እና ጸጥታ” ናቸው ብለዋል።
አንቶኒ ብሊንከን፤ በዛሬው እለት ምርጫ በማካሄድ ላይ ያለችውን ኬንያ አንስተው ሲናገሩም፤ "አፍሪካ ችግሮች ያሉባት፤ አሜሪካ ደግሞ መፍትሄ ሰጪናት" ብለው እንደማያስቡ ፤ ነገር ግን በጋራ በመሆን ችግሮችን ለመፍታት ለሚደረጉ ጥረቶች አሜሪካ እውቅና እንደምትሰጥ አስረድተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሊቢያ፣ ማሊ እና ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ስለሚገኙና የ“ዋግነር” ቡድን በመባል ስለሚታወቁ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ያላቸው አስተያየትም ሰንዝረዋል።
ብሊንከን፡ በክረምሊን የሚደገፈው የ“ዋግነር” ቡድን፤ " በአለመረጋጋት ውስጥ ሃብትን የሚዝቅና በደል የሚፈጽም ቡድን ነው" ሲሉ ከሰውታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ላለው የዋጋ ንረት ዋና ምክንያት ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ነው ለሚለው ክስም ምልሽ ሰጥተዋል።
ብሊንከን በሰጡት ምልሽ "ፕሬዝዳንት ፑቲን ወረራ ከመጀመራቸው በፊትም ቢሆን ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ 193 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር" የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።
ያም ሆኖ የዓለም ባንክ ከነበረው 193 ሚሊዮን በተጨማሪ በጦርነቱ ምክንያት ለ40 ሚልዮን ህዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ያሰፈልጋል ባለው መሰረት፤ አሜሪካ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሀገራት ስትደግፍ፤ ሩሲያ ግን ችግር በመፍጠር ላይ መሆኗ ተናግረዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ቆይታ ያደረጉት ብሊንከን ቀጣይ ጉዞዋቸውን ወደ ሩዋንዳን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ መሆኑ ተገልጿዋል።
ብሊንከን በአፍሪካ ቆይታቸው በምግብ ደህንነት ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ንግድ እና ጤና ጉዳዮች ዙሪያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
አንቶኒ ብሊንከን የአሁኑ የአፍሪካ ጉብኝት ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ባሳለፍነው ህዳር ላይ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል እና ኬንያን ጎብኝተው መመለሳቸው ይታወሳል።