ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ዶ/ር ቴድሮስን ተጠያቂ ማድረጋቸው ሰፊ ተቃውሞ አስተናገደ
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ዶ/ር ቴድሮስን ተጠያቂ ማድረጋቸው ሰፊ ተቃውሞ አስተናገደ
ከሰሞኑ በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረ ኢየሱስና በሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ዘመቻዎች እየተደረጉ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ በድርጅቱ ወረርሽኝ ተብሎ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ በየዕለቱ በዓለም ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ያሉት መረጃዎች የሚለዋወጡበት መግለጫ እየተሰጠ ነው፡፡ በመግለጫውም አሁን ላይ ያለውን የቫረሱን የስርጭት ሁኔታ፣ የጥንቃቄ መልዕክቶችና ሌሎችንም ከዋና መስሪያ ቤቱ ጅኔቫ ሆኖ እየገለጸ ነው፡፡
ተቋሙ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጭ ቡድኖችን በየአህጉሩ ያሰራጨ ቢሆንም ለቻይና እንዳደላ፣ ቫይረሱንም ቀድሞ አላጋለጠም የሚሉ ወቀሳዎች በአክቲቪስቶችና በመሪዎች እየተደረጉበት ነው፡፡ ከሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነው ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ መስፋፈት ጣታቸውን በድርጅቱ ላይ በመቀሰር ተጠያቂ አድርገውታል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ወቀሳ ምን ይላል?
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ሃገራቸው ለድርጅቱ ከፍተኛ ገንዘብ እንደምታዋጣ በመጠቆም ድርጅቱ ደግሞ ለቻና ያደላ ነው የሚል ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ ሀገራቸው ለድርጅቱ የምታደርገውን የገንዘብ ድጎማ እንደምታቆምም ማሳሰቢያ ጭምር ልከዋል፡፡
‹‹የዓለም ጤና ድርጅት ቫረሱን ለመከላከል የተከተለው አመራር ደካማ ነው፤ ለቻይና ያደላ ተቋም ሆኗል›› ያሉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ለድርጅቱ የምትሰጠውን ገንዘብ ልታቆም ትችላለች›› ሲሉ ቃል በቃል ጽፈዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይና ያደላና አገልግሎቱም ቻይናን ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑ የገለጹ ሲሆን ይህም ዋሸንግተንና ቤጅንግ የንግድ ጦርነቱን አሁን በክፉ ቀንም አልረሱትም ወይ አስብሏል፡፡
ከዚህም ባለፈ አሜሪካ ከቻይና የሚደረጉ በረራዎች እንዲቋረጡ በወሰነጭ ወቅት ዶ/ር ቴድሮስ መቃወማቸውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተችተዋል፡፡ የቻይናን መረጃ ብቻ በመውሰድ የዓለም ጤና ድርጅት እንድንዘናጋ አድርጎናልም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ድጋፍ
ይህንን የትራምፕን ዘመቻ ተከትሎም የአፍሪካ ሕብረትና የአባል ሃገራቱ መሪዎች ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ድጋፋቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ከአሜሪካ በዓለም ጤና ድርጅት አመራር ላይ እየተደረገ ያለውን ዘመቻ አውግዟል፡፡ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ትናንት በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው እንደገለጹት አሁን ላይ ዓለም አቀፉን ወረርሽን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ በሚያስፈልግበት ወቅት ከአሜሪካ በኩል ይህንን መስማታቸው እንዳስገረማቸው ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ሙሳ የአፍሪካ ሕብረት ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጎን እንደሚቆምና ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን የኮሚሽነሩን ሃሳብም የኢትዮጵያ፣ የሩዋንዳ፣ ሴኔጋልና የሌሎች ሃገራት መሪዎች ተቀላቅለዋል፡፡ መሪዎቹ ‹‹አሁን ወረርሽኙን የመከላከያ ጊዜ እንጂ ተጠያቂነትንና ወቀሳን የምናወራበት ጊዜ አይደለም›› ብለዋል፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛም በትናንትናው እለት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን አሞካሽተዋል፡፡ ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ዶ/ር ቴድሮስ ጠንካራ አመራር በመስጠት ወረርሽኙን ለመከላከል ከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጡ እንደሚገኙ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡ መላው ዓለም ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ሊሰራ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስለወቅታዊው ዘመቻ ምን አሉ?
የዓለም ጠየና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ትናንት በሰጡት መደበኛ መግለጫ በእርሳቸው ላይ በግል የሚቀርቡ ዘመቻዎች ከሦስት ወራት በፊት መጀመራቸውን አስታውቀው ይህ ብዙም እንደማያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም አሁን ላይ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ላይ ሙሉ ትኩረታችን ቫረሱን መከላከል ላይ ነው፣ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ሃገራት በጋራ መቆም አለባቸው፣ በየደቂቃው ሰዎች እየሞቱ ነው፣ ይህንን ደግሞ ፖለቲካ ማድረግ ነውር ነው›› ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የያኔዋ ሶቪየት ህብረትና አሜሪካ ያን ያህል ልዩነት እያላቸው በወቅቱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ግን በጋራ ይሰሩ እንደነበር ለአብነት በማንሳት አሁንም አሜሪካና ቻይና ልዩነትን ወደጎን በመተው ወረርሽኙን መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እርሳቸውን በሚመለከት የሚቀርቡ ትችቶች ፈጽሞ እንደማያሳስባቸው ገልጸው ይህንን ምንጊዜም መቀጠል ይቻላል፤ በማህበረሰብ ደረጃ የሚደረጉ ትንኮሳዎችና ዘለፋዎችን ግን በቃ ማለት ይገባል ብለዋል፡፡ ጥቁር በመሆኔ እኮረራለሁ፣ የበታችነትም አይሰማኝም ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በርካታ ህይወት እየጠፋ ነው ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ የሰው ልጆችን ህይወት ለማትረፍ የቡድን 20 አባል ሃገራትና ሌሎችም በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡ በእርሳቸው ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎች ከሦስት ወራት በፊት መጀመራውንና መነሻቸውም ታይዋን መሆኗን አንስተዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸው ስህተቶች ሊሰሩ ይችላሉ፤ ይሁንና ከስህተቶችና ከጥንካሬዎች እንማራለን ብለዋል፡፡