16 ሚስቶች፣ 104 ልጆች እና 144 የልጅ ልጆች ያሏቸው ታንዛኒያዊ "የአባቴን አደራ" አልበላሁም አሉ
አዛውንቱ ሁሉንም ቤተሰብ ማስተዳደር ቢችሉም የልጆቻቸውን ስም ማስታወስ ግን እንደከበዳቸው ይናገራሉ

ከሚስቶቻቸው ውስጥ ሰባቱ እህትማማቾች ሲሆኑ 40 ልጆችን በህመምና በአደጋ አጥተዋል
እንኳን ጎጆ ቀልሶ እና ልጆች ወልዶ አንድ ራስን ማስተዳደር በከበደበት በዚህ ወቅት ታንዛኒያዊው አዛውንት 16 ሚስቶችን አግብተው ቤተሰባቸውን ማስፋት ላይ ተጠምደዋል።
ጆምቤ በተባለች ትንሽ መንደር ነዋሪ የሆኑት ኤርኔስቶ ሙኑቺ ካፒንጋ 104 ልጆችና 144 የልጅ ልጆቻቸውን እንደ አንድ ቤተሰብ በማስተዳደር ላይ ናቸው።
የራሳቸውን ቤተሰብ መንደር የመሰረቱት ካፒንጋ ሁሉም ሚስቶቻቸው የራሳቸው ቤት እንዲኖራቸው አድርገዋል።
ካፒንጋ በቅርቡ ከአፍሪማክስ ጋር ቃለምልልስ ሲያደርጉ ከአንድ በላይ ሚስት እንዲያገቡ የወተወቷቸው አባታቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።
በፈረንጆቹ 1961 የመጀመሪያ ሚስታቸውን ያገቡት አዛውንቱ ከአንድ አመት በኋላ የመጀመሪያ ልጃቸውን አግኝተዋል። የልጅ ልጅ ማየታቸው ያስደሰታቸው የካፒንጋ አባት ልጃቸውበአንድ ሚስት እንዳይወሰንና ተጨማሪ ሚስቶችን የሚያገባ ከሆነ ለባል የሚሰጠውን ጥሎሽ ራሳቸው እንደሚከፍሉም ቃል ይገባሉ።
አባቴ "የኛ ጎሳ ትንሽ ስለሆነ ላስፋፋው እፈልጋለው" አሉኝ የሚሉት ካፒንጋ የአባታቸውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ይተጉ ጀመር። የመጀመሪያ አምስት ሚስቶቻቸውን ጥሎሽ አባታቸው ችለውም ቤተሰቡ እየተስፋፋ መጣ። በዚህ ግን አልቆመም። የአባታቸውን ምክር የሰሙት ካፒንጋ የሚስቶቻቸውን ቁጥር 20 አደረሱት( አራቱ በሞትና በፍቺ ቢለዩዋቸውም)።
በአሁኑ ወቅት 16 ሚስቶች አሏቸው፤ 104 ልጆችና 144 የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል።
የአዛውንቱ የተከበረ ስምና ዝና፤ ሁሉንም በእኩል የሚመለከቱበትና ለችግሮች የሚሰጡት ሚዛናዊ መፍትሄ ሰባት እህትማማቾች እንዲያገቡቸው እስከማድረግ ደርሷል።
"ሁሉም ሚስቶቼ የራሳቸው ቤት፣ የማብሰያ ክፍል ስላላቸው ምንም ፉክክር የለም፤ ሁሉም የራሳቸውን ስፍራ ያውቃሉ፤ በጋራ ሰርተን በጋራ እንመገባለን፤ ይሄ ቤት ብቻ አይደለም፤ ስርአትም ጭምር ነው" ሲሉም ይናገራሉ።
ይህን ቤተሰብ ማስተዳደር አልከበደዎትም ወይ? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም ሁሉም የእርሻ መሬት ስላላቸውና ከብት ስለሚያረቡ ገቢ አያሳስበንም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ካፒንጋ እና ሚስቶቻቸው በቆሎ፣ ባቄላ፣ ካሳቫ፣ ሙዝ እያመረቱ ከፍጆታ ተርፎ ለሌሎች ነገሮች መሸመቻ ይሸጣሉ።
"ሰዎች እኔ ሁሉንም ነገር እንደምቆጣጠር ያስባሉ፤ እውነታው ግን ሴቶቹ ናቸው ቤተሰቡን በአንድነት የሚመሩት፤ እኔ ዋናው ስራዬ ይህን ማስተባበር ነው" ይላሉ አዛውንቱ።
ሚስቶቻቸውም የሚገጥማቸውን ማንኛውም ነገር ለባላቸው በግልጽነት እንደሚናገሩና ሁሉንም በእኩልነት የሚያደምጡት ካፒንጋም ለአንዱ ሳያደሉ መፍትሄ ማስቀመጣቸው ቤተሰቡ እስካሁን በሰላም እንዲኖር ማድረጉን ተናግረዋል ብሏል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ።
ኤርኔስቶ ሙኑቺ ካፒንጋ አንድ ነገር ግን ከብዷቸዋል፤ የልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ስም ማስታወስ። እስከ 50ኛ ያሉትን ልጆቻቸውን በደምብ የሚያስታውሱት አዛውንት የቀሪዎቹን 64 ልጆች ግን ስም ለመጥቀስ ግን ፊታቸውን መመልከት ይኖርባቸዋል።
ካፒንጋ 40 ልጆቻቸውን በህመምና አደጋ አጥተዋል። ቀሪ በርካታ ልጆቻቸው ግን የእርሳቸውን መኖር ይሻሉና ሀዘናቸውን ችለው የአባታቸውን ተልዕኮ ማስፈጸምን ተያይዘውታል።