12 ሚስቶች ፣ 102 ልጆች እና 578 የልጅ ልጆች ያሏቸው ኡጋንዳዊ አባወራ
በምስራቃዊ ኡጋንዳ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት የ70 አመት አዛውንት ቤተሰባቸውን መመገብ ፈተና ሆኖባቸዋል
ግለሰቡ ቤተሰባቸው ከመስፋቱ የተነሳ ከመጀመሪያ እና የመጨረሻ ልጆቻቸው በስተቀር የልጆቻቸውን ስም እንደማያስታውሱ ይናገራሉ
ሙሳ ሀሳህያ ካሴራ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በምስራቃዊ ኡጋንዳ ሙኪዛ መንደር ሲሆን የ70 አመቱ አዛውንት ሰፊ ቁጥር ባለው ቤተሰባቸው የመገናኛ ብዙሀን መነጋገርያ ሆነው ቆይተዋል፡፡
የሃሳህያ ታሪክ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች በብዛት መሰራጨቱን ተከትሎ “በአለም ላይ ብዙ ልጆችን የፈጠሩ ሰው” በሚል ስያሜ በዓለም ዙሪያ መነጋገርያ ሆነዋል፡፡
12 ሚስቶች ፣ 102 ልጆች እና 578 የልጅ ልጆች ያሏቸው አባወራ ከቤተሰባቸው መስፋት የተነሳ ምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ፈተና እንደሆነባቸው እየተነገረ ነው፡፡
በ1972 የመጀመሪያ ሚስታቸውን በ17 ዓመታቸው ያገቡት አባወራው ባለፉት አሥርተ ዓመታት በከብት ነጋዴነት እያደገ የመጣው ሀብታቸው የመንደሩ ነዋሪዎች ከሀሳህያ ጋር በጋብቻ ለመዛመድ ሴት ልጆቻቸውን እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡
ቀስ በቀስ12 ከደረሱ ሚስቶቻቸው 102 ልጆችን የወለዱት አዛውንቱ በአሁኑ ወቅት የልጆቻቸው እድሜ ዝቅተኛው 10 ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 50 ነው፡፡
አዛውንቱ አባወራ “የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ልጄን ስም ብቻ ማስታወስ እችላለሁ፣ የሌሎቹ ግን ስማቸውን ማስታወስ አልችልም” ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የቤተሰባቸው በዚህ ልክ መስፋት በረከትም ሸክምም እንደሆነባቸው የሚናገሩት ሙሳ ሀሳህያ ካሴራ የቤተሰቡ ቁጥር እያደገ በሄደ ቁጥር በእጃቸው ላይ ያለው ሀብት እና ጥሪት እንዲመናመን ስለማድረጉ ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚኖሩትም ጣራው በዛገ እና በሳር በተሸፈኑ የጭቃ ጎጆዎች ውስጥ ሲሆን በአንድ ወቅት ሙሉ ቤተሰቡን ለመደጎም በቂ ነው ተብሎ ይታሰብ የነበረው ሁለት ሄክታር መሬት ከመሰረታዊ ድጎማ እምብዛም የዘለለ እገዛ እንደሌለው ተዘግቧል፡፡
በዚህ የተነሳም አባወራው ለቤተሰባቸው በቀን ለአንድ ግዜ ወይም ከሁለት ጊዜ በላይ መመገብ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሀሳህያ ለኤፍፒ እንደተናገሩት “መጀመሪያ ላይ ሁኔታዎች ቀልድ እና ከቁጥጥር ውጪ የሚሆኑ አይመስሉም ነበር፤ አሁን ላይ ግን ልጆቼ የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን ሰርተው የሚያገኙት ገቢ እና ከመኖሪያ ቤት ግንባታ በቀረችው ስፍራ ላይ የምንዘራው ፍሬም የሚሰጠው ምርት ሙሉ ቤተሰቡን ለማስተዳደር በቂ አይደለም” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ካላፈው ሀላፊነት ካልተሞላበት ውሳኔየ ብዙ ተምሬያለሁ የሚሉት አዛውንቱ አባወራ በአሁኑ ወቅት ሌላ ልጅ ላለመውለድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡