የዝንጅሮ ፈንጣጣ ክትባት በመጪዎቹ ቀናት በአፍሪካ እንደሚጀመር የአፍሪካ ሲዲሲ አስታወቀ
በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቱ 19 ሺህ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል
የአለም ጤና ድርጅት ስርጭቱ በኮሮና ልክ እንደማይሆን ገልጿል
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ በአፍሪካ እንደሚጀመር የአፍሪካ ሲዲሲ አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ባወጣው መረጃ እንደገለጸው በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የክትባት እጥረት ቢኖርም ስርጭቱ ያየለባት አፍሪካ ቅድሚያ ይሰጣታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የክትባቱ ውድነት በርካታ ሀገራት ገዝቶ የማቅረብ አቅም ስለሌላቸው በቂ አቅርቦት እንዳይኖር እክል መፍጠሩ ሲነገር በአሁኑ ወቅት የአንድ ዶዝ ክትባት ዋጋ 100 ዶላር መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ጄን ካስያ እስከ መጪው ሳምንት ድረስ በሽታውን ለመቆጣጠር እቅድ መውጣቱን የተናገሩ ሲሆን ስርጭቱ በሚገኝበት ሁኔታ ዙሪያ ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በመጪዎቹ ቀናት 200ሺ ዶዝ ክትባት ለድርጅቱ እንደሚቀርብ እና ተጨማሪ 10 ሚሊየን ዶዝ ክትባት እንደሚስፈልግ ነው የገለጹት፡፡
የአውሮፓ ህብረት እና የኔዘርላንዱ የክትባት አምራች ባቫሪያን ኖርዲክ ለአፍሪካ የክትባት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
በሽታው በንክኪ ፣ በጾታዊ ግንኙነት ፣ ልብስ በመጋራት እና በሌሎችም መንገዶች ይተላለፋል፡፡
እራስ ምታት ፣ ሰውነት ላይ የሚከሰቱ እብጠቶች ፣ ትኩሳት ፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡
ባለፈው ሳምንት ብቻ በመላው አፍሪካ 1400 አዳዲስ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም በመላው አህጉሪቱ የሚገኙ የተጠቂዎችን ቁጥር 19 ሺህ አድርሶታል፡፡
የዘንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የጤና ስጋት ነው ብሎ ያወጀው የአለም ጤና ድርጅት በሽታው የኮቪድ 19ን ያህል ሰርጭቱ ተጽዕኖ እንደማይኖረው አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ በተጨማሪ በስዊዲን አንድ ታማሚ ተገኝቷል። ፊሊፒንስ እና ታይላንድ በተመሳሳይ በቅርቡ ወደ አፍሪካ የጉዞ ታሪክ ባላቸው ዜጎቻቸው ላይ በሽታው መገኝቱን አስታውቀዋል፡፡