በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው የተጻፈ ደብዳቤ ለክልሉ የመንግስት መዋቅሮች ተልኳል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማያውቀው ማንኛውንም ስብሰባ በክልሉ የሚገኙ መዋቅሮች እንዳያደርጉ ከለከለ።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ለዞን ፣ ለወረዳ ፣ ለክፍለ ከተማ አስተዳደሮችና ለወረዳ ምክር ቤቶች ተልኳል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የትኛውም መዋቅር አስፈላጊ ስብሰባዎችን የሚያደርግ ከሆነ ከጊዜያዊ አስተዳደሪ ጋር በቅድሚያ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚኖርበት ነው በደብዳቤው ላይ የተመላከተው፡፡
በተጨማሪም የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው የሚገኙ ጉዳዮችን አስቀምጧል፡፡
እነርሱም "የኮሌራ በሽታ መከላከል ፣ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው መመለስና የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስከበር ፣ የ2016 ዓ.ም በጀት መዝጋትና የ2017 ዓ.ም በጀት ማዘጋጀት ሲሆኑ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ ሰብሰባዎች የተያዘው እቅድ ስለሚጎዱ አይፈቀዱም "ብሏል።
ከዚህ ውጪ የሚጠራ ማንኛውም አይነት ስብሰባ ተቀባይነት እንደሌለው የገለጸው ደብዳቤው፤ የክላስተር አስተባባሪዎች እና የክልሉ ቢሮዎች ቁጥጥር እና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ከሰሞኑ በሁለት በተከፈሉ የህወሓት አመራሮች ምክንያት የትግራይ ክልል ውጥረት ውስጥ እነደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገውን 14ኛ የድርጅት ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው በዶክተር ደብረዲዮን የሚመራው ህውሓት ቡድን ስብሰባውን ባጠናቀቀበት ወቅት የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች በስብሰባው ያልተሳተፉ አመራሮችን ከሀላፊነት ማንሳቱን ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡
የዶክተር ደብረጺዮን በአቶ ጌታቸው ምትክ አቶ አማኑኤል አሰፋን የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን ሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንም በአዲስ ተክቷቸዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ፕሬዝዳነት አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልከቶ ባለፈው ቅዳሜ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “የሚመራ ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመንጠቅ ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል” ተናግረው ነበር።