በ42 ዓመቱ ጎል ካስቆጠረው ሮጀር ሚላ በግራ እግሩ ኳስን እስከሚያናግረው አል ሃጂ ዲዩፍ ተጠቃሽ ናቸው
በ42 አመቱ ጎል ካስቆጠረው ሮጀር ሚላ በግራ እግሩ ኳስን እስከሚያናግረው አል ሃጂ ዲዩፍ አፍሪካ ድንቅ ችሎታ ያላቸው ልጆቿን በአለም ዋንጫው አስተዋውቃለች።
54 ሀገራት መገኛዋ አፍሪካ በአለም ዋንጫ የምታሳትፈው አምስት ሀገራትን ብቻ ነው። አውሮፓ በአንፃሩ 55 ሀገራትን ይዛ 13 ሀገራትን እንድታሳትፍ ተፈቅዶላታል።
ከአስሩ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አራት ወይ አምስቱ በየአራት አመቱ የኳስ ደረጃቸውን የሚፈትሹበት አለም አቀፍ መድረክ ያገኛሉ።
ይህን ኢፍትሃዊነት የምትቃወመው አፍሪካ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የእግር ኳስ እድገቷ ወደኋላ የቀረ ቢሆንም በተፈጥሮ ብቃታቸውን አለምን ያስደመሙ ተጫዋቾች መፍለቂያ ናት።
የአለም ዋንጫ ሲነሳም ክስተት የሆኑ አንፀባራቂ ልጆቿ የፈፀሙት አይረሴ ታሪክ ማውሳት ተገቢ በመሆኑ የተወሰኑትን እነሆ፦
ኢማኑኤል አሙንኬ
ጉዳት የማያጣው ናይጀሪያዊው ኢማኑኤል አሙንኬ በ1994ቱ የአለም ዋንጫ ስብራቱን ያስረሳ ድንቅ ብቃት አሳይቷል።
ሀገሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችበትን የአለም ዋንጫ በጎል አስጀምሯል። ጣሊያን እና ቡልጋሪያ ላይ ጎል አስቆጥሮ ሀገሩን ብሎም አፍሪካን ከቁዘማ አላቋል።
ዳኔል አሞካቺ፣ ፊንዲ ጆርጅ እና ረሺድ ይኪኒን ያካተተው ብሄራዊ ቡድን ምስራቅ አውሮፓዊቷን ቡልጋሪያ 3 ለ 0 በማሸነፍ ወርቃማ ድል ሲያስመዘገብ ኢማኑኤል አሙንኬ ፈር ቀዳጁን ጎል ከመረብ አገናኝቷል።
ከጣሊያን በተደረገው ግጥሚያም አሙንኬ ለንስሮቹ መሪ ያደረገች ጎል አስቆጥሮ ነበር (ሮቤርቶ ባጆ በ76ኛውና 102ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ቢሸነፉም)።
ንስሮቹ አሜሪካ ባስተናገደችው የአለም ዋንጫ ጉዟቸው በአጭር ቢገታም እንደነ ጄጄ ኦኮቻ አይነት ድንቅ ተጫዋቻቸውንም አስተዋውቀውናል።
አሳሟህ ጂያን
"ህፃኑ ጄት" በአለም ዋንጫው የተከሰተው በፈረንጆቹ 2006 ነው፤ ጋና ጀርመን ባዘጋጀችው የ2006ቱ የአለም ዋንጫ ስትሳተፍ።
በመክፈቻው በጣሊያን የገጠማቸውን የ2 ለ 0 ሽንፈት ቼክ ሪፐብሊክን በተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ ሲገለብጡ ጁያን እና ሱሊ ሙንታሪ ጎሎቹን ማስቆጠራቸው የሚታወስ ነው።
አሜሪካን 2 ለ 1 በመርታት 16 ውስጥ ሲገቡም ጂያን ወሳኝ ጎል አግብቷል። ደቡብ አፍሪካ በ2010 ባዘጋጀችው የአለም ዋንጫም ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ስሙን በደማቁ አፅፏል።
በሩብ ፍፃሜው ፍልሚያ የኡራጋዩ ልዊስ ስዋሬዝ ባለቀ ስአት ሆን ብሎ ኳስ በእጁ ነክቶ ለጋና የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት መሳቱና ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከግማሽ ፍፃሜው ውጭ መሆኗ ግን ጥቁር ጠባሳን ጥሎበት አልፏል።
አሳሟ ጂያን በ2014ቱ የብራዚል የአለም ዋንጫ በፓርቹጋል ላይ ጎል በማስቆጠር በአለም ዋንጫው ያስቆጠራቸውን ጎሎች 6 በማድረስም፤ የጋናም ሆነ የአፍሪካ ሪከርዱን ይዟል።
ከ12 አመት በፊት የሳተው ፍፁም ቅጣት አሁንም ድረስ ከአዕምሮው ያልወጣው የ36 አመቱ ጂያን ኳታር ላይ ብሄራዊ ቡድኔን ተቀላቅዬ ታሪክ ልስራ የሚል ጥሪ አቅርቦ ነበር።
4ኛ የአለም ዋንጫ ተሳትፏቸውን በኳታር በሚያደርጉት ጥቋቁሮቹ ከዋክብት ያልተካተተው የአፍሪካ ኮከብ በአንድ ምድብ የሚያገኟትን ኡራጓይ እንዲያሸንፉለት እየተጠባበቀ ነው።
ኤል ሃጂ ዲዩፍ
በግራ እግሩ ኳስን የሚያናግረው አል ሃጂ ዲየፍ በአፍሪካ ከአይረሴ ተጫዋቾች በግምባር ቀደምነት ይነሳል። ሴኔጋል ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ባዘጋጁት የ2002ቱ የአለም ዋንጫ ፈረንሳይን ያሸነፉበት ጨዋታ በአለም የእግር ኳስ ታሪክ አይዘነጋም።
የቴራንጋ አናብሰቶቹ ላጣጣሙት ድል ዲዩፍ ብቸኛዋን ጎል ከማስቆጠር ባሻገር ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ ላይ ያሳየው ችሎታ አለምን ቁጭ ብድግ አስብሏል።
የነዜነዲን ዚዳን ሀገር ለሴኔጋል የወረደ ግምት ሰጥታ ተጫዋቾቹም ልምምድ አላደረጉም። የፓሪስ ጋዜጦችም 8 ለ 0 እናሸንፋለን ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዲዩፍ ግን የቴራንጋ አናብስቶቹን አባላት የነጄጄ ኦኮቻን የነሮጀር ሚላን ስኬት እያነሳ ቡድኑን አበርትቶ ያልተጠበቀው ሆነ። በፈረንሳዊው ብሩኖ ሜትሱ የምትሰለጥነው ሴኔጋል በአል ሃጂ ዲዩፍ የ30ኛ ደቂቃ ጎል አሸነፈች። ይህን ጨዋታ የተመለከቱት የአውሮፓ ክለቦችም የአፍሪካውን ኮከብ ለማስፈረም ተረባርበውበታል።
ሮጀር ሚላ
በ42 አመቱ ጎል ያስቆጥራል፤ በተጨማሪ ስአት ኳስን ከመረብ በመቀላቀልም ይታወቃል - ሮጀር ሚላ። ጎል ሲያገባ ወደ ማዕዘን ሄዶ የሚያሳየው ትዕይንትም በርካቶች ኮርጀውት አሁንም ድረስ ሲጠቀሙበት ሚላ ይታወሳል።
ሶስት ጊዜ አረንጓዴውን መለያ ለብሶ ለካሜሮን የተጫወተው ሮጀር ሚላ በ1990ው የአለም ዋንጫ (በ38 አመቱ) አራት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ኮሎምቢያ ላይ ባለቀ ስአት ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ካሜሮንን ከአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለች ሀገር ያደረገውም ይሄው እድሜ ያላቆመው ተጫዋች ነው።
በ1994ቱ የአለም ዋንጫም ከተጠባባቂነት ተነስቶ (በ42 አመቱ) ጎል በማስቆጠር ሌላ ታሪክ አፅፏል። የማይበገሩት አንበሶች በአለም ዋንጫው ተጠባቂ ይሆኑ ዘንድ ፈገግታ ከፊቱ የማይጠፋው ሮጀር ሚላ ወሳኝ ድርሻ ነበረው።
የአለም ዋንጫ ሲቃረብ የጠቀስናቸው የአፍሪካ ከዋክብት ደማቅ ታሪክ ይወሳል። በኳታሩ የአለም ዋንጫም የአሁኖቹ ከቀደምቶቹ የአሸናፊነት ወኔና ብቃትን ወርሰው ከተሳትፎ ያለፈ ውጤት እንዲያሳዩ ይጠበቃል።