የዓለም ዋንጫ የምንጊዜም ምርጥ 10 የእግር ኳስ ተጫዋቾች
የኳታር የ2022 የአለም ዋንጫ ሊጀመር 7 ቀናት ቀርተዋል፤ የእርሶ የምንጊዜም የእግር ኳስ ተጫዋች ማነው?
ፕሌ፣ ማራዶና፣ ዬሃን ክራይፍ፣ ሮናልዶ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ልብ የማይጠፉ ከዋክብት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው
የአለም ዋንጫ ሲቃረብ ከብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ልብ የማይጠፉ ከዋክብት ስም ይነሳል።
የምንጊዜም 10 ተጫዋቾች ዝርዝር ሲወጣም አጨቃጫቂነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በየአራት አመት የአለም ዋንጫ ሲደረግ ኮከቦቹ ደማቅ ታሪካቸው ይታወሳል።
አል አይን አማርኛም የኳታር የአለም ዋንጫ መቃረቡን ተከትሎ የምንጊዜም 10 የአለም ዋንጫ አንፀባራቂ ተጫዋቾችን ሊያወሳ ይወዳል።
10. ዜነዲን ዚዳን
ፈረንሳዊው ዚዙ ሀገሩ ባዘጋጀችው የ1998 የአለም ዋንጫ በፍፃሜው ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ዋንጫ አንስቷል።
108 ጊዜ ተሰልፎ 31 ጎሎችን ያስቆጠረው ዚዳን፥ በአወዛጋቢነቱ ይበልጥ ይታወቃል።
በተለይ ጀርመን ባዘጋጀችው የ2006ቱ የአለም ዋንጫ ማርኮ ማታሬዚን በቴስታ የመታበት ክስተት አሁንም ድረስ ከትውስታ ማህደር አይጠፋም።
ሪያል ማድሪድን በማሰልጠን ሶስት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች ያነሳው ዚዙ የአለም ዋንጫ ሲነሳ ሁሌም ከነአይረሴ ክስተትነቱ ይወሳል።
9. ጂሚ ግሪቭስ
ዌምብሌይ ስታዲየም ላይ ሃውልት ከቆመለት ቦቢ ሞር በላይ እንግሊዛዊያን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች እንደ ጂሚ ግሪቭስ የሚሳሱለት ተጫዋች የለም።
ግሪቭስ የ1966ቱን የአለም ዋንጫ ያነሳው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አባል ነው፤ ነገር ግን ፈረንሳዊው ጆሴፍ ቦኔል ያደረሰበት ጉዳት ከፍፃሜው ውጭ አድርጎታል። ጉዳቱ ከ14 በላይ ቦታ እንዲሰፋ ማስገደዱን መረጃዎች ያወሳሉ።
ግሪቭስ የእንግሊዝን መለያ ለብሶ ስድስት ሃትሪክ በመስራት ክብረ ወሰኑን እንደያዘ ነው።
እነግሪቭስ የ1966ቱን የአለም ዋንጫ አዘጋጇ ሀገራቸው የተለየ የእግር ኳሷ ቀለም እንዳላት አሳይተውበታል።
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውንም በ2009 የአለም ዋንጫ ሜዳል ለጂሚ ግሪቭስ አበርክተዋል።
8. ፑሽካሽ
ፈረንስ ፑሽካሽ ለሀንጋሪ 85 ጨዋታዎችን አድርጎ 84 ጎሎችን ያስቆጠረ ድንቅ ተጫዋች ነው።
በ1950ዎቹ የአውሮፓ ድንቅ የነበረው ፑሽካሽ በ705 ጨዋታዎች 702 ጎሎችን በማስቆጠርም የሚስተካከለው አላገኘም።
የ1956ቱን የሀንጋሪ አቢዮት ደግፎ ወደ ስፔን ተሰዶ ለስፔን ብሄራዊ ቡድን አራት ጊዜ መሰለፉም ከአነጋጋሪ ጉዳዮቹ መካከል ይጠቀሳል።
የኮሙዩኒዝም ስርአት ሲገረሰስ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ፑሽካሽ አሁንም ድረስ በሀንጋሪያውያን ልብ ትልቅ ስፍራ አለው።
ለአለም የእግር ኳስ አበርክቶውም በስሙ የተሰየመ ሽልማት በየአመቱ ይሰጣል፤ ከፈረንጆቹ 2009 ወዲህ የአመቱ ምርጥ ጎል በፑሽካሽ አዋርድ እውቅና እየተሰጠው ነው።
7. ሎታር ማትሀውስ
የአለም አቀፉ የእግስ ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ብሎ የሸለመው ብቸኛ ጀርመናዊ ማትሀውስ ነው።
በአምስት የአለም ዋንጫዎች የተሳተፈው አማካይ 150 አለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለሀገሩ አድርጓል፤ በ25 የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ለሀገሩ በመሰለፍ እስካሁን ድረስ ክብረወሰኑን እንደያዘ ነው።
ቡድን የመምራትና ታክቲክ የመረዳት ልዩ ብቃት የተላበሰው ማትሀውስ የሜዳ ንጉስ ነው ይሉታል።
ዲያጎ ማራዶናም እንደ ማትሀውስ ያለ ጠንካራ ተጫዋች አልገጠመኝም ብሎ የኋላ መስመር ደጀንነቱን መስክሮለታል።
6. ሚሮስላቭ ክሎስ
ፈጣኑ ጀርመናዊ አጥቂ የአለም ዋንጫን ከሚያስናፍቁ ተጫዋቾች አንዱ ነው።
ለሀገሩ 137 ጊዜ ተሰልፎ 71 ጎሎችን ከመረብ ያዋሃደው ክሎስ፥ አይተኬ አጥቂነቱን አስመስክሯል።
በአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ያስመዘገበው 16 ጎልም በአውሮፓዊቷ ሀገር ትልቁ ነው።
በአራት የአለም ዋንጫ ተሳትፎ የ2014ቱን ዋንጫ የሳመው ክሎስ ከፍጥነቱና ኳስ አዋቂነቱ ባሻገር በአመለ ሸጋነቱም የተመሰከረለት ነው።
ክሎስ በ2012 ለጣሊያኑ ለላዚዬ ሲጫወት ናፖሊ ላይ ጎል አስቆጥሮ እንዲሻር ጠይቋል፤ በእጄ ነክቻለሁ ብሎ ሀቁን በመናገር።
ከዚሁ አስገራዊ ጎሌ ይሻርልኝ ጥያቄው ሰባት አመታት ቀደም ብሎም የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አልመታም ማለቱ መነጋገሪያ ነበር።
ምናልባት ዳኛው ተሳስተው ይሆናል እንጂ ምንም ጥፋት አልተሰራብኝም በማለት ጨዋነቱንና ፍትሃዊ ውጤት ፈላጊነቱን አሳይቷል።
5. ሮናልዶ
"ክስተቱ" አለምን ከጫፍ ጫፍ በእግር ኳስ ፍቅር አሳብዷል።
በ17 አመቱ የ1994ቱን የአለም ዋንጫ ያነሳው ምትሃተኛ፥ ለደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገሩ ብራዚል 98 ጊዜ ተሰልፎ 62 ጎሎችን አስቆጥሯል።
በ2002 ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በጋራ ባዘጋጁት 17ኛው የአለም ዋንጫ ባለቁንጮው ሮናልዶ ልዊስ ናዛሪዬ ደ ሊማ ኮከብ ነበር፤ በፍፃሜው ሁለት ጎሎችን ጀርመን ላይ አስቆጥሮ ሀገሩን የለመደችውን ድል አጎናፅፏታል።
በአራት የአለም ዋንጫዎች ላይ የተሰለፈው ተወዳጅ ተጫዋች 15 ጎሎችን በማስቆጠር የወቅቱን ክብረ ወሰን ይዞ ነበር።
ኳስ አያያዝ፣ እንደ ፈንጂ የሚወነጨፍ ፍጥነት፣ እየተገለባበጠ የሚያገባቸው ጎሎች እና ተከላካዮችን የሚያልፍበት ጥበብ ሮናልዶን አሁንም ተናፋቂ ያደርጉታል።
4. ፍራንዝ ቤከንባወር
የትኛውም የአለም ዋንጫ 10 የምንጊዜም ተጫዋቾች ዝርዝር ቤከንባወርን አይዘልም።
ተከላካዩ ቤከንባወር ለያኔዋ ምዕራብ ጀርመን 14 ጎሎችን አስቆጥሯል።
በ1966ቱ የአለም ዋንጫ ከእንግሊዝ ጋር ለፍፃሜ ደርሰው 4 ለ 2 መሸነፋቸው ያንገበገበው ቤከንባወር፥ ከአራት አመት በኋላ ሀገሩ እንግሊዝን ጥላ ግማሽ ፍፃሜውን እንድትቀላቀል በማድረግ ቁጭቱን አብርዷል።
በመሪነት ብቃቱ "ደር ኬይሰር" ወይም ንጉሱ እያሉ የሚጠሩት ፍራንዝ አንቶን ቤከንባወር፥ የሀገር ሸክምን ብቻውን በጫንቃው የሚሸከም ብርቱ ሰው መሆኑንም ይመሰክሩለታል።
በግንብ አጥር የተለያዩት ምዕራብ እና ምስራቅ ጀርመን ሲዋሃዱም ቤከንባወር ቡድኑን እየመራ የ1990ውን የአለም ዋንጫ አንስቷል።
3. ዬሃን ክራይፍ
የሶስት ጊዜ የባለንዶር አሸናፊው ዬሃን ክራይፍ በአለም ዋንጫውም ሆነ በአጠቃላይ የእግር ኳሱ አለም ተፅዕኖ ከፈጠሩ ግለሰቦች ከፊት ከሚቀመጡት ውስጥ ነው።
ክራይፍ ከተሰለፈ ሀገሩ ኔዘርላንድስ አትሸነፍም፤ በ48 አቀፍ ጨዋታዎች ተሰልፎ 33 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ብርቱካናማዎቹ ደቾች በ1974 ከምዕራብ ጀርመን ጋር ለፍፃሜ ሲደርሱ ክራይፍ ትልቅ ድርሻ ነበረው፤ አርጀንቲና ላይ ሁለት ጎሎችን ከማስቆጠር ባሻገር ለወቅቱ ሻምፒዬን ብራዚል ፈተና ሆኗል።
ክራይፍ በጀርመናዊው ፍራንዝ ቤከንባወር እንደ አለት የጠነከረ መከላከል ተፈትኖ ዋንጫውን ቢያጣም የወቅቱ አቋሙ አሰደናቂ ነበር።
የዬሃን ክራይፍን ኳስ አዋቂነቱን፣ የአሰላለፍ ታክቲክ ክህሎቱን የሚያደንቁ ከመራሂ ኦርኬስትራ ጋር ያመሳስሉታል።
ደቻዊዉ የኳስ ጠቢብ ከግብ ጠባቂው በስተቀር ሁሉንም ተጫዋቾች አጥቂ የሚያደርግ ቶታል ፉትቦል (ቲኪ ታካ) የተሰኘ የኳስ ፍልስፍናን አስተዋውቋል።
ኳስ እንዲሁ የአትሌቲክስ ስፓርት ሳይሆን የአዕምሮ፣ ሰውነት እና ጥበብ ውህደት የሚታይበት ቀለል ያለ ሆኖ ግን ውበት የተሞላበት ሊሆን ይገባል በሚል አስተያየታቸውም ይታወቃሉ።
2. ማራዶና
"ወርቃማው ልጅ" ምድራችን ካፈራቻቸው የምንጊዜም ተጫዋቾች ቀዳሚው ነው።
በ1986ቱ የአለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ አምስት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን ሸውዶ አልፎ (60 ሜትር) ያስቆጠራት ጎል የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ተሰኝታለች።
"የእግዜር እጅ" የሚላት በእጁ ያስቆጠራት ግብም ከዲያጎ አርማዶ ማራዶና ጋር ተያይዛ ሳትነሳ አታልፍም።
ማራዶና ለነጭና ሰማያዊ ለባሾቹ 91 ጊዜ ተሰልፎ 34 ጎሎችን አስቆጥሯል።
የኮኬይን እፅ ጋር በተያያዘ በ1991 በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የእግር ኳስ ህይወቱ የተበላሸው ማራዶና፥ በ1994ቱ የአለም ዋንጫ የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሙ በመረጋገጡ መታገዱ ይታወሳል።
አንፀባራቂው ኮከብ፥ የአሜሪካን የኢራቅ ወረራ በመቃወም፤ የቼ ጉቬራ እና ፊደል ካስትሮን ስም መነቀስ ይቻላል በሚሉና በሌሎችም አነጋጋሪ አስተያየቶች ይታወቃል።
ሁጎ ቻቬዝ በ2007ቱ የኮፓ አሜሪካ ውድድር የክብር እንግዳ ይሁኑ የሚለው ንግግሩም የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ነበር።
1. ፔሌ
በ1958ቱ የአለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጎሉን ዌልስ ላይ ሲያስቆጥር ፔሌ ከእውቅና ማማ ይደርሳል ዌልስም ለሰባት አስርት አመታት የአለም ዋንጫን ተመኝታ ትቀራለች ብሎ የገመተ አልነበረም።
ፔሌ በምትሃተኛ እግሮቹ ተአምር ባሳየባቸው የ1958፣ የ1962 እና 1970 የአለም ዋንጫን አንስቷል፤ በ92 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው 77 ጎሎችም አሁንም ከብራዚል የግብ አነፍናፊዎች ከፊት የሚያስቀምጡት ናቸው።
ፔሌ ለቡድን አጋሮቹ በነበረው አክብሮትና ለጎል ሳይስገበገብ በማቀበል ይታወቃል፤ ለጥቁሮች መብትም ተቆርቋሪነቱን አሳይቷል።
የፔሌ ተወዳጅነት ጦርነት እስከማስቆም ይደርሳል፤ በ1969 የናይጀሪያ የእርስ በርስ ጦርነት የቆመው ፔሌ ሌጎስ በመገኘት እንዲጫወት ከተስማማ በኋላ ነው።
"ኳስ በፔሌ እግር ከነሙሉ ክብሯ ትታያለች" በሚለው ብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ይስማሙበታል።
የኳታሩ የአለም ዋንጫ የዘመኑን ፔሌና ማራዶናን ያሳየን ይሆን?