በቆራጥና ፍትሃዊ ዳኝነት የሚታወቁት የአለም ዋንጫው ተናፋቂ - ፔርሉጂ ኮሊና
በ2002ቱ የአለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን በድንቅ ብቃት በመምራት ጎልተው የወጡት ኮሊና ፥ ዳኝነት እንዲከበር ያለፍርሃት ትክክለኛ ውሳኔ መስጠትን በተግባር አሳይዋል
የሚፈሩት ዳኛ በአለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ስድስት ጊዜ በተከታታይ የአመቱ ምርጥ ዳኛ ሆነው ተመርጠዋል
የአለም ዋንጫ ሲደርስ ጣሊያናዊው ዳኛ ፔርሉጂ ኮሊና ከነቆፍጣና ውሳኔያቸው ይታወሳሉ።
ራሰ በራው፤ ባለሰማያዊ አይኑ ዳኛ የዳኝነት ተምሳሌት ሆነው አሁንም ድረስ ከፊት ይቀመጣሉ።
በተወለዱበት ቦሎኛ ኳስ እየተጫወቱ ያደጉት ኮሊና ደንቅ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ህልም ነበራቸው።
ይሁን እንጂ የገጠማቸው ፀጉራቸውን የሚበጣጥስ ህመም ከህልማቸው ሊለያያቸው ተደነቀረ።
በቦሎኛ ዩኒቨርሲቲ የዳኝነት ሰርተፊኬት በ17 አመታቸው የወሰዱት ኮሊና ፥ በኢኮኖሚክስም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ቢይዙም ወደ ህይወት ጥሪያቸው ትኩረት አድርገዋል።
እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ባይችሉም የሜዳው ንጉስ ሆኑ።
በሰፈር ጨዋታ የተጀመረ ኮስታራና ሀቀኛ ዳኝነታቸው በጣሊያን ሴሪአ ተጀምሮ ለትልቁ የአለም የእግር ኳስ መድረክ በቁ።
ኮሊና ከሻምፒዬንስ ሊግ እስከ የአውሮፓ እና የአለም ዋንጫ ያልዳኙት ትልቅ ጨዋታ የለም።
ኮሊና የ1999ኙን የማይቸስተር ዩናይትድ እና ባየር ሙኒክ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜን ሲዳኙ በበርካቶች አይን ገብተዋል።
በ2002 ጃፓን ባዘጋጀችው የአለም ዋንጫ የጀርመን እና ብራዚል የፍፃሜ ጨዋታ በፍፁም ቆራጥ ውሳኔ ከመሩ በኋላም ዝናቸው ናኝቷል።
የተጫዋቾችን ጥፋት የማይታገሱት ጣሊያናዊ ግን ሁሌም ፍትሃዊ ናቸው ይባልላቸዋል።"ዳኝነትን እንደ ሙያ ማስከበር እፈልጋለው፤ ሁሌም ወደ ሜዳ ስገባ ላመነብኝ መታመኔ ግድ ነው፤ በፍርሃት ሳልሸበብና ለማንም ሳላዳላ እወስናለሁ" ይላሉ ኮሊና።
አለም ዋንጫን መዳኘት ከባድ መሆኑን የሚናገሩት ታማኙ ዳኛ፥ እንቅልፍ ያጡባቸው የአለም ዋንጫ ምሽቶች በርካታ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
ይህ ሙያ አክባሪነታቸው በተጫዋቾች የተከበሩ እና የሚፈሩ በአሰልጣኞች እና በጠቅላላው ስፖርት ወዳድም ተናፋቂ አድርጓቸዋል።
ለዚህ ታማኝነታቸውም የአለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ለስድስት ጊዜ በተከታታይ የአመቱ ምርጥ ዳኛ ብሎ መርጧቸዋል።
ኮሊና በቆፍጣና ውሳኔያቸው ከወታደር ጋር የሚያመሳስሏቸው በርካታ ናቸው።
ከአራት በላይ ቋንቋ መናገራቸውም ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ለመግባባት እንደረዳቸው ነው የሚነገረው።ለ28 አመት የዘለቀው የዳኝነት ሙያቸው በ2005 በ45 አመታቸው ተደምድሟል።
አለም ዋንጫ ሲደርስም ጣሊያናዊው ፔርሉጂ ኮሊና ከነኮስታራ ፊታቸው ይወሳሉ።