ክርስቲያኖ ሮናልዶን ይዛ ወደ ዓለም ዋንጫ የምትጓዘው የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት ምን ይመስላል?
ፖርቹጋል በምድብ 8 ከጋና፣ ኡራጓይ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ተመድባለች
ኳታር የምታስተናግደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ሊጀመር 9 ቀና ቀርተውታል
ከፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ጋር ስሙ እኩል የሚነሳው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ እንደሚሆን ተገምቷል።
በአውሮፓ መድረክ የ2016ቱን የአውሮፓ ዋንጫ ከማንሳት የዘለለ ትልቅ ታሪክ ያላፃፉት “ሴሌሳዎ ዳስ ኪናስ” (ቅፅል ስማቸው)፤ በዓለም ዋንጫው የረባ የስኬት ታሪክ የላቸውም።
ጀርመን ካስተናገደችው የ2006 አለም ዋንጫ ወዲህ ሩብ ፍፃሜ መድረስ አልቻሉም። ብራዚል ከ1950 ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀችው የአለም ዋንጫም ከምድባቸው ማለፍ ሳይችሉ ወደ ሊዝበን መመለሳቸውም አይዘነጋም።
"አይገመቴዎቹ" ባለፉት ሶስት የአለም ዋንጫዎች ያሸነፉት ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው። የአለም የእግር ኳስ ኮከቡ ክርስቲያኖ ሮናልዶም አለም ዋንጫ ላይ ኳስና መረብን ማገናኘት ከባድ ሆኖበታል።
ፖርቹጋል እና የአለም ዋንጫ
የቀደመ የአለም ዋንጫ ተሳትፎ - 7
የወሰደችው ዋንጫ - 0
ጥሩ አጨራረስ - በ1966 እና 2006 ግማሽ ፍፃሜ መድረስ
በአለም ዋንጫው ያስመዘገበችው - 14 ድል፣ 6 አቻ እና 10 ሽንፈት
የተመዘገበ ጎል - 49
በሰፊ ልዩነት ያሸነፈችበት ጊዜና ውጤት - 7 ለ 0 (በ2010 ሰሜን ኮሪያን)
ግሩም ተጫዋቿ - ክርስቲያኖ ሮናልዶ
አሁናዊ አለም አቀፍ የእግር ኳስ ደረጃ - 9ኛ
የምድብ ተፋላሚዎቿ - ጋና፣ ኡራጓይ እና ደቡብ ኮሪያ
ምድብ 8
ፖርቹጋል በምድብ 8 ከጋና፣ ኡራጓይ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ተመድባለች።
ጋናን በብራዚሉ የ2014 የአለም ዋንጫ፤ ኡራጓይን ደግሞ 2018 ላይ በሩስያ ያሸነፉት ጎራዴዎቹ፤ ከምድባቸው የማለፉ ቀዳሚው ግምት ተሰጥቷቸዋል።
ቼክ ሪፐብሊካዊው አሰልጣኛቸው ፌደሪኮ ሳንቶስ ቡድናቸው በኳታር የተለየ ብቃቱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ከጥቋቁሮቹ ከዋክብት ጋር ማድረጋቸውም መልካም እድል ይዞ እንደሚመጣ ባለፉት የአለም ዋንጫዎች የነበራቸውን የበላይነት በማጣቀስ እየገለፁ ነው።
ሮናልዶና የአለም ዋንጫ
የተሳተፈባቸው የአለም ዋንጫዎች ብዛት - 4 (የኳታሩን ሳይጨምር)
የተሰለፈባቸው ጨዋታዎች - 17
ያገባው ጎል - 7 ሲሆን፤ 2006 (1)፣ 2010 (1)፣ 2014 (1)፣ በ2018 (4)
ባለፈው አመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለማንቸስተር ዩናይትድ 24 ጎሎችን ያስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ፥ ከአሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሃግ ጋር መስማማት ተስኖት ከጨዋታ ርቋል።
የሀገሩ ብሄራዊ ቡድን ግን ተስፋውን በሱ ላይ አድርጓል።
የአትሌቲኮ ማድሪዱ ጆኦ ፌሊክስ እና የኤሲ ሚላኑ ራፋኤል ሊዎ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር የፊት መስመሩን ይቆጣጠራሉ። የማንቸስተር ከተማ ተቀናቃኝ ክለቦች አማካዮች በርናንዶ ሲልቫ እና ብሩኖ ፌርናንዴዝም የማጥቃቱን ሂደት እንዲያግዙ ይጠበቃል።
የእነ ልዊስ ፊጎ እና ዴኮ ሀገር ፖርቹጋል አሁንም የአጥቂ ችግር እንደሌለባት ቢነሳም ቀዳሚ ተመራጩ 38 አመት ሊሞላው የተቃረበውን ሮናልዶ ነው።
የአራት ጊዜ ባሎንዶር አሸናፊው፤ ከ800 በላይ ጎሎችን በማስቆጠር ክብረወሰን የያዘው ሮናልዶ በተሰለፈባቸው ያለፉት 10 የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ያስቆጠረው 5 ጎሎችን ነው፤ እነዚህ ጎሎችም በሁለት ጨዋታዎች የተቆጠሩ ናቸው።
ቁጥሮች ምንም ይናገሩ ሮናልዶ በመጨረሻ የአለም ዋንጫ ተሳትፎው የተሻለ ውጤታማ እንዲሆን የሚመኙለት የስፖርት ወዳጆች በርካታ ናቸው።