የአፍሪካ ህብረት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ አድርጎ በቅርቡ ሾሞ ነበር
ኦባሳንጆ አፍሪካን የሚያውቁ፤ ለአፍሪካ ክብር ያላቸው፤ ጥበብና ብልሃት ያላቸው ትልቅ ሰው ናቸው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በጸጋ ተቀብለነዋል ብለዋል።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት ካስፈለገ ኦባሳንጆን መሠል ሰዎች ያስፈልጉናልም ነው አምባሳደር ዲና ያሉት።
ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ተሾሙ
ስራ ሲጀምሩ ተገናኝተን ልንወያይ እንደምንችል ተስፋ እናደርጋለንም ነው ቃል አቀባዩ ያሉት። ኦባሳንጆ በእኛ ጉዳይ ገንቢ ሚና ይጫወታሉም ብለን እናስባለንም ብለዋል።
ኦባሳንጆ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ነው ከቀናት በፊት የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ሆነው የተሾሙት።
ሹመቱ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮች ለማየትና ለመፍታት ጭምር በሚያስችል መልኩ የተደረገ ስለመሆኑ ይነገራል።
ሆኖም የህብረቱን ገለልተኛነት ያጠየቀው ህወሓት ሹመቱን አልተቀበለውም።
ይህ ህወሓት “ለአፍሪካ ክብር እንደሌለው፤ ለአፍሪካ መሪዎች እውቅና እንደማይሰጥ እና ለፈረንጅ ያለውን አክብሮት” ነው የሚያሳየው እንደ አምባሳደር ዲና ገለፃ።
በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ሲባል ኢትዮጵያን ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነና ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮችም እንዳሉ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
በእነዚህና በእኛ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ሚና ይጫወታሉ፤ ወደ ስራ በሚገቡበትም ሰዓት ተገናኝተን በጋራ ጉዳዮች ላይ እንነጋገራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል ቃል አቀባዩ።