ጠ/ሚ ዐቢይ በግድቡ የድርድር ጉዳይ ላይ ከወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ጋር ተነጋገሩ
ሺስኬዲ በሱዳን እና ግብጽ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ መግባታቸው የሚታወስ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺስኬዲ በድርድሩ ሂደት በመጫወት ላይ ስላሉት ሚና አድንቀዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የወቅቱን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የዲ.አር ኮንጎውን ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺስኬዲን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በፕሬዝዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት መደሰታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግድቡ ድርድር እየተጫወቱ ስላለው ሚና አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካ ህብረት መር በሆነና ለሁሉም በሚሰራ ስምምነት ቁርጠኛ ሆና እንደምትቀጥልም ነው የገለጹት፡፡
ጽህፈት ቤታቸው ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት መካከል የትብብርና የጋራ ልማት ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል እና በሁለቱም ሀገራት ላይ ምንም ጉዳት በማያስከትል መንገድ እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያላትን ጽኑ አቋም ስለማስረዳታቸው አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በትብብር መርህ ማዕቀፍ (ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ) መሠረት ለሁሉም ወገኖች የሚጠቅም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያላትን ፍላጎት ደግማ ትገልጻለችም ነው ጽህፈት ቤቱ ያለው፡፡
ፌሊክስ ሺስኬዲ በሱዳን እና ግብጽ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ጠዋት ነው አዲስ አበባ የገቡት፡፡
ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜም የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሺስኬዲ አመጣጥ ለጊዜው የተቋረጠውን የግድቡን የሶስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል እና ስምምነት ላይ መድረስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡