አፍሪካውያን ወጣቶች በሀገራቸው ያላቸው ተስፋ እየተሟጠጠ ነው - ጥናት
የግላቸውን ህይወት ለማቃናት ጥረት የሚያደርጉትም ስደትን ዋነኛው ከችግር መውጫ መንገድ ማድረጋቸውን ጥናት አመላክቷል
በጥናቱ የተሳተፉት አብዛኞቹ ወጣቶች በዴሞክራሲ ስርአት ቢያምኑም ጥቂት የማይባሉ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትን ድግፈዋል
የ2022 የአፍሪካ ወጣቶች የዳሰሳ ጥናት የአህጉሪቱ ወጣቶች በሀገራቸው የመኖርና የመበልጸግ ተስፋቸው እየወረደ መሆኑን አመላክቷል።
ሊቺኮዊዝ ፋሚሊ ፋውንዴሽን እድሜያቸው ከ18 እስከ 24 የሆኑ 4 ሺህ 500 ወጣቶችን በአካል ቃለመጠይቅ አድርጎ የሰራውን ጥናት ይፋ አድርጓል።
ጥናቱ አብዛኞቹ የአፍሪካ ወጣቶች በሀገራቸው የነገ ተስፋቸው የተሻለ ይሆናል ብለው አያምኑም ይላል።
ሶስት አራተኛው የጥናቱ ተሳታፊ ወጣቶችም ትኩረታቸው የግል ህይወታቸውን ማስተካከል ላይ ብቻ እንዲሆን እንደሚፈልጉ ነው ጥናቱ የጠቆመው።
የፋይናንስ ችግር እና ውድ የሆነ የኢንተርኔት ዋጋ ምኞታቸውን እውን እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሆነባቸውም የጥናቱ ተሳታፊ ወጣቶች ያነሳሉ።
አፍሪካውያን ወጣቶች ስለኑሮ ደረጃ ያላቸው አመለካከትም ከ2019 ወዲህ በ10 ነጥብ መቀነሱ ተመላክቷል።
በሀገራቸው ጥሩ ኑሮ የመምራት ተስፋቸው እየተመናመነ የመጣው የአፍሪካ ወጣቶች ስራ ለማግኘትና ትምህርታቸውን ለመቀጠል በቀጣይ ሶስት አመታት ወደ ሌላ ሀገር መሰደድን እንደመረጡም ያክላል።
በተለይ የዜጎች እኩልነት የማይከበርባቸው፣ የስራ እድል ፈጠራ በተዳከመባቸው፣ የፖለቲካ መርጋጋት በራቃቸው ሀገራት የወጣቶች የወደፊት ተስፋ እጅጉን መውረዱን ነው ጥናቱ ያሳየው።
በጥናቱ ከተሳተፉት ወጣቶች ውስጥ 74 ከመቶው ዴሞክራሲ ተመራጭ የመንግስት አስተዳደር ስርአት መሆኑን ያምናሉ፤ ነገር ግን 35 ከመቶው ብቻ ናቸው አፍሪካ የምዕራባውያንን የዴሞክራሲ ስርአት መከተል አለብን ያሉት።
22 ከመቶው ደግሞ ሀገራቸው መፈንቅለ መንግስት በሚያደርጉ ወታደሮች ብትተዳደር መርጠዋል።
ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትን ከደገፉት የአፍሪካ ወጣቶች ሱዳን (37 በመቶ)፣ ጋቦን (33 በመቶ) እና ጋና (32 በመቶ) በመያዝ ይመራሉ።
ካርቱም በመንግስት ግልበጣ ወደስልጣን የመጣውን ወታደራዊ አስተዳደር በሚቃወሙ ስልፈኞች አደባባዮቿ ሲጨናነቁ መዋላቸው ግን አሁንም አልቆመም።
የሊቺኮዊዝ ፋሚሊ ፋውንዴሽን ጥናት በአፍሪካ አህጉር ከአሜሪካ ይልቅ ቻይና ተጽዕኖ ፈጣሪና ተመራጭ መሆኗንም አሳይቷል።
ቤጂንግን ከየትኛውም የአለም ሀገርና ተቋም በበለጠ በአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናት ያሉት ወጣቶች 77 ከመቶውን ይይዛሉ፤ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ፈረንሳይና ሩስያ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
76 በመቶ ወጣቶች ቻይና በአህጉሪቱ ያላትን ተሳትፎ በበጎው የሚመለከቱ ናቸው ተብሏል።
ቻይና ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ምርቶችን ማቅረቧ እና የስራ እድል የሚፈጥሩ መሰረት ልማቶችን መገንባቷም በወጣቶቹ በስጋትነት ሳይሆን በተስፋ ፈንጣቂነት እንድትታይ ማድረጉን ነው አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ያስነበበው።
70 በመቶ ህዝቧ ወጣት ያለባት አህጉር በልጆቿ የነገ እጣፈንታዋን ለማሳመር ከፈለገች የታዳጊ እና ወጣቶቿን ተስፋ ማለምለም አለባት።
በጥናቱ የተጠቀሱት የወጣቶች ስራ ፈጠራ ማነቆዎች ካልተፈቱም ትውልዱ ስደት ናፋቂ ሆኖ ይቀራል ነው ያለው ሊቺኮዊዝ ፋሚሊ ፋውንዴሽን።