አፍሪካዊቷ ሞሮኮ የቀድሞ ቅኝ ገዥዋን ፈረንሳይ ትገጥማለች
በአለም ዋንጫው አስገራሚ ጉዞ ያደረጉት የአትላስ አናብስቱ የሁለት ጊዜ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮኖቹን ሰማያዊ ለባሾች ይረቱ ይሆን?
የተጫዋቾች የጉዳት ዜና በሁለቱም በኩል እየተነሳ ነው
የአለም ዋንጫ በ1930 ከተጀመረ ወዲህ ዋንጫውን ስምንት ሀገራት እየተፈራረቁ አንስተዋል።
24 የተለያዩ ሀገራትም ለግማሽ ፍጻሜ መድረሳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ ከደረሱ ሀገራት 25ኛዋ ሆና ዛሬ ምሽት 4 ስአት ፈረንሳይን ትገጥማለች።
የአትላስ አናብስቱ ቤልጂየም፣ ስፔንና ፖርቹጋልን እየጣሉ ለፍጻሜው መድረሳቸው ጠንካራ የድል ብርታትን ይፈጥርላቸዋል።
እስካሁን አንድ ጎል ብቻ ያስተናገደው ቡድን ጠንካራ የተከላካይ መስመሩም ይነሳለታል።
የአልባይት ስታዲየሙ ፍልሚያ የፓሪሰ ሴንት ጀርሜን ተጫውቾቹን ኪሊያን ምባፔ እና አሽራፍ ሃኪሚ ያፋጥጣል።
በኳታር አምስት ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን የሚመራው ምባፔ ከሌላኛው የሀገሩ ልጅ ኦሊቨር ጂሩድ ጋር በመጣመር የሞሮኮን የግብ ክልል ይፈትናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕ የተከላካይ መስመር ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ጉዳት ማስተናገዳቸው ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ተሰግቷል።
በሞሮኮም በኩል አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጊ እስካሁን ከምሽቱ ጨዋታ ውጭ የሆነ ተጫዋች የለም ቢሉም ሮማይን ሲያስ እና ናይፍ አጉይርድ ጉዳት ላይ ናቸው ተብሏል።
ፈረንሳይ በመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያዎቿ (በ1958፣ በ1982 እና በ1986) ተሸንፋ ከዋንጫ ፉክክር ውጭ ሆናለች። በ1998፣ 2006 እና 2018 ደግሞ አሸንፋ ለፍጻሜ በቅታለች። ከዚህ ውስጥ ሁለቱን ማሳካት (1998 እና 2018) ችላለች።
በስድስተኛ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋ በፊፋ የአለም የእግርኳስ ደረጃ ከፊት የተቀመጡትን ሃገራት አሸንፋ ለግማሽ ፍጻሜው የደረሰችው ሞሮኮ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሀገር በመሆን ታሪክ አጽፋለች።
በአለም ዋንጫው መድረክ ተገናኝተው የማያውቁት ሞሮኮ እና ፈረንሳይ በዛሬው የግማሽ ፍጻሜ ትንቅንቅ ይፋለማሉ።
በመጪው እሁድም ከአርጀንቲና ጋር የዋንጫ ፍልሚያ የሚያደርገው ሃገር ይለያል።
በየቀኑ ወደ ዶሃ እየገቡ የሚገኙ የሞሮኮ ደጋፊዎችም እንደተለመደው የአልባይት ስታዲየምን ያደምቁታል ተብሎ ይጠበቃል።
የእርሶስ ግምት ምንድን ነው?