“ፈጣሪን ለማሳየት” 1 ሺህ 600 ዶላር ክፍያ የጠየቀው የደቡብ አፍሪካ ፓስተር
ፓስተሩ ብድራቸው እንዲሰረዝላቸው የሚፈልጉ ምዕመናን 5 ሺህ ራንድ (290 ዶላር) መክፈል አለባቸው ብሏል
580 ዶላር የከፈለ ደግሞ በአምልኮው ቀን ማግስት ማግባት እንደሚችል ነው የሚገልጸው
በአፍሪካ ተአምራትን እናሳያለን እያሉ ገንዘብ የሚሰበስቡ “ነብዮች” እየተበራከቱ ነው። ከወደ ደቡብ አፍሪካ የተሰማው ዜናም በሃይማኖት ስም የሚነግዱ ሰዎች የደረሱበትን የማጭበርበር ጥግ ያሳያል።
“ፈጣሪን በገነት ለማየት ከፈለጋችሁ 1 ሺ 600 ዶላር መክፈል አለባችሁ” ያለው ፓስተርም የሰሞኑ መነጋገሪያ መሆኑን ኦዲቲ ሴንተራል በድረ ገጹ አስነብቧል።
ኤምኤስ ቡደሊ የተባለው ፓስተር፥ ምዕመናን ክፍያ መፈጸም ከቻሉ የማይታመን የሚመስሉ ተአምራቶችን ማሳየት እችላለሁ ባይ ነው።
ፌስቡክ ላይ ያሰፈረው ለተአምራቱ የሚያስከፍለው የዋጋ ዝርዝርም በማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃውሞ አስነስቶበታል። ቡደሊ በስማርት ስልኮች መጻኢ እድላቸውን ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች መፍትሄው በጄ ነው ብሏል።
“እዳችሁን ማሰረዝ የምትፈልጉም ወደኔ ኑ” የሚል መልዕክቱን አጋርቷል። “ፈጣሪን መመልከት” የሚፈልጉ ምዕመናንም በፈረንጆቹ ታህሳስ 25 2022 በሚያደርገው የአምልኮ ጉባኤ እንዳይቀሩ ተጋብዘዋል።
በባዶ እጅ ወደ አምልኮው ቦታ መሄድ ግን ከተአምራቱ ጋር አያገናኙም።
“በገነት እግዚአብሄርን ለመመልከት” 20 ሺህ ራንድ ወይም 1 ሺህ 600 ዶላር መክፈል ግዴታ ነው።
ብድራቸው እንዲሰረዝላቸው የሚፈልጉ ምዕመናን ደግሞ 5 ሺህ ራንድ (290 ዶላር) እንዲከፍሉ ዋጋ ወጥቶለታል።
በአምልኮው ቀን ማግስት ለማግባት የፈለገ ሰው 10 ሺ ራንድ መክፈል ይኖርበታል ይላል ቡደሊ የለጠፈው የቅሰቀሳ ፖስተር።
በስማርት ስልኮቻቸው መጻኢያቸውን መመልከት ያሰኛቸው ወገኖችም 1 ሺህ 660 ዶላርን ይከፍሉ ዘንድ ተጠይቀዋል።
የሃይማኖት አባት ነኝ የሚለው ቡደሊ “ፈጣሪን በገነት ከማሳየት” 15 እጥፍ ዋጋ የጠየቀው አቬየተር የተሰኘውን ታዋቂ የኦንላይን ጌም ማሸነፍ ለሚፈልጉ ምዕመናን ነው፤ 17 ሺህ 400 ዶላር መክፈል ጌሙን አሸናፊ ያደርጋል ይላል።
ይህ በፖስተር ላይ የተለጠፈ የአምልኮ ጉባኤ እና የተአምራት ዋጋ ዝርዝር በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ከፍተኛ ነቀፌታ ደስሮበታል።
“ይህ የለየለት ቅጥፈት ነው” ፤ የሚሰረዝ እንዳም ሆነ በስማርት ስልክ የምንመለከተው ነገ አይኖርም” የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችም በተለጠፈው ምስል ስር ተሰጥተዋል።
“ነገሩን በየዋህነት የሚያዩ ምስኪን ቤተሰቦቻችን የሚሳካ መስሏቸው ወደ ቡደሊ ሊሄዱ እንደሚችሉ አልጠራጠርም” ያለ አንድ አስተያየት ሰጪም እንዲህ አይነት የእምነት ነጋዴዎችን የልብ ልብ የሚሰጠው ንቃተ ህሊናው ዝቅ ያለ ምዕመን ነው የሚል ሃሳብ አስፍሯል።
በደቡብ አፍሪካ በ2019 “የሞት ሰው አስነሳለሁ” ያለው ፓስተር ኤልፍ ሉካኦ ያልሞተን ስው እንደሞተ አድርጎ በማስነሳት ምዕመናንን በመሸወዱ ዘብጥያ መውረዱ ይታወሳል።
በዚምባቡዌም “ከፈጣሪ ጋር በስልክ እናወራለን” ያለው ፓስተር ፖል ሳንያንጎሬ በቴሌቪዥን ጣቢያ “ቀጥታ ከገነት” የሚል ፕሮግራም ሊጀምር መሆኑንና “የፈጣሪን ስልክ ቁጥር ይፋ አደርጋለሁ” ሲል መደመጡ አይዘነጋም።