የሳዑዲ ሴቶች በቅርቡ ባቡር መሾፈር ይጀምራሉ ተባለ
ሪያድ በዓመት እስከ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ በማሰብ ከመካ እስከ መዲና የፈጣን ባቡር መስመር መዘርጋቷ ይታወሳል
ሳዑዲ ሴት የባቡር ሹፌሮችን ለማሰልጠን ማስታወቂያዎችን አውጥታለች
የሳዑዲ አረቢያ ሴቶች በቅርቡ የሃገሪቱን ፈጣን የከተማ ባቡር መሾፈር ይጀምራሉ ተባለ፡፡
ሴቶቹ በቅርቡ ከመካ መዲና የተዘረጋውን የሃራማይን ፈጣን የከተማ ባቡር መሾፈር ይጀምራሉ ተብሏል፡፡
በእስልምና ሃይማኖት በቅዱስነት የሚጠቀሱትን ከተሞች የሚያገናኘው የሃራማይን ፈጣን የባቡር መስመር በዓመት እስከ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ታስቦ መገንባቱ ይነገርለታል፡፡
ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን የሚደርሱ የሃጅ እና ዑምራ ተጓዦችን ሊያጓጉዝ እንደሚችል ታስቦ የተገነባም ነው፡፡
በፈረንጆቹ 2018 ስራ ጀመረው ባቡር መስመሩ 483 ኪሎ ሜትሮችን ይረዝማል፡፡
ሴቶቹም ይህን በሰዓት 300 ኪሎ ሜትሮችን የሚምዘገዘገውን ባቡር በቅርቡ መሾፈር እንደሚጀምሩም ነው የተነገረው፡፡
የሃገሪቱ የባቡር አገልግልት ተቋም ሴት ሾፌሮችን (ኮንዳክተርስ) ለማሰልጠን ማስታወቂያ ማውጣቱንም አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ማስታወቂያው ለአንድ ዓመት የሚቆ ነው፡፡
የተቋሙ ስራ አስኪያጅ የሳዑዲ ሴቶች በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡