አሜሪካ፤ ሶማሊያ ምርጫን በተያዘለት ጊዜ የማታካሂድ ከሆነ “እርምጃ እወስዳለሁ” በማለት አስጠነቀቀች
ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ ማስጠንቀቅያው “በደስታ እንቀበላለን” ሲሉ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ አስተያየት ከመሰጠት ተቆጥበዋል
የፖለቲካ ተንታኞች ማስጠንቀቅያው የሶማሊያ ፖለቲካ ውስብስብነት የሚያመላክት ነው ብለዋል
አሜሪካ፤ ሶማሊያ ምርጫን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ የማታካሂድ ከሆነ እርምጃ እንምትወስድ አስጠነቀቀች።
ሶማሊያ በቅርቡ የተስማማችውን ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ካላሟላች ማዕቀብ እንደሚጣልባትም የአሜሪካው የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በትዊተር ገጹ ላይ ማስጠንቀቅያ አዘል መልእክቱን ያጋራው።
እንደ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘገባ፡ ቢሮው "የሶማሊያ ምርጫ ከታቀደለት ከአንድ አመት በላይ ዘግይቷል፤ እናም አሁን ላይ አዲሱ የብሔራዊ የምክክር ምክር ቤት የጊዜ ሰሌዳ የማይሟላ ከሆነ አሜሪካ በአጥፊዎች ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተዘጋጅታለች”ም ብሏል፡፡
የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሁሴን ሮብሌ፤ በቃል አቀባዩ መሀመድ ኢብራሂም ሙአሊሙ በኩል ለአናዶሉ ኤጀንሲ በሰጡት አስተያየት “የአሜሪካን ማስጠንቀቅያ በደስታ እቀበላለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባራቸውን ለመወጣት እና ሀገሪቱን ወደ ሰላማዊ ምርጫ ለመምራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
"መግለጫውን በደስታ እንቀበላለን እና የተዘጋጀውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የጣሰ ሰው ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ተስማምተናል"ም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አክለዋል።
የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ ፡የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ መሀመድ/ ፋርማጆ/ ለስድስት ቀናት የዘለቀው የብሄራዊ የምክክር ምክር ቤት ስብሰባ ውጤትን እና የታችኛው ምክር ቤት ምርጫ እስከ የካቲት 25 ድረስ እንዲጠናቀቅ የደረሱትን ስምምነት እንደሚቀበሉ ካሳወቁ በኋላ የመጣ ነው።
ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ መሀመድ /ፋርማጆ/ በአሜሪካ ማስጠንቀቅያ ዙሪያ እስካን አስተያየት አለመስጠታቸውም ታውቋል።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ ማስጠንቀቅያ የሶማሊያ ፖለቲካ ምን ያህል አስቸጋሪና ውስብስብ እየሆነ እንደመጣ የሚያሳይ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች በመግለጽ ላይ ናቸው።