ችግር ላይ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ የሚመክር ልዑክ ከሰሞኑ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናል ተባለ
በኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ አዲስ ድባብ መታየቱ ተገልጿል
ልዑኩ ከሳምንት ባልበለጡ ቀናት ውስጥ ወደ ሪያድ ሊያቀና እንደሚችል አምባሳደር ዲና ተናግረዋል
ችግር ላይ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ የሚመክር የኢትዮጵያ ልዑክ ከሰሞኑ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናል ተባለ፡፡
በሳዑዲ አረቢያ ህይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ እየመሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ መንግስት ይረዳል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ችግሮቹን ለመፍታት ያለመ ልዑክ ወደ ሪያድ እንደሚያቀና ተናግረዋል።
ልዑኩ መቼ ወደ ሪያድ ያቀናል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም "ምን አልባት በአንድ ሳምንት ውስጥ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል አምባሳደሩ።
“ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ ከአገሪቱ መንግስት ጋር በመመካከር በሳውዲ ችግር ላይ ያሉ ዜጎቻችን ወደ አገራቸው መመለስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መምከር ዋነኛ ተልዕኮው ይሆናል”ም ብለዋል አምባሳደር ዲና።
ቃል አቀባዩ አክለውም በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጫና እየቀለለ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
ጫናው የቀለለው በህወሓት ላይ በተወሰደው እርምጃ፣ ዳያስፖራዎች ባደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት እና በየአህጉሪቱ ያሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ባደረጉት ጥረት እንዲሁም የብሄራዊ ምክክር ሂደቱ በመጀመሩ መሆኑም ተገልጿል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ ድባብ በማሳየት ላይ እንደሆነም አምባሳደር ዲና አክለዋል።
መንግስት ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም ሲል ሰሞኑን የተወሰኑ እሥረኞችን ክስ አቋርጦ አቶ ስብሃት ነጋን፣ አቶ ጃዋር መሃመድን እና አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌች የተወሱ እስረኞችን መፍታቱ የሚታወስ ነው።
ተመድ እና አሜሪካ እርምጃው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት የተደረገ በጎ ጅምር ነው ሲሉ ማወደሳቸው አይዘነጋም፡፡