በድህረ ብሬግዚት እንግሊዛዊ ሆነው መቀጠል እንደማይፈልጉ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር አባት አስታወቁ
ወግ አጥባቂው ፖለቲከኛ በወላጅ እናታቸው በኩል ፈረንሳዊ መሆናቸውን ጠቁመዋል
የ80 ዓመት አዛውንቱ ስታንሌይ ጆንሰን ፈረንሳዊ የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወላጅ አባት ስታንሌይ ጆንሰን ፈረንሳዊ ዜጋ የመሆን ውጥን እንዳላቸው አስታወቁ፡፡
የ80 ዓመቱ አዛውንት ይህን ያሉት በልጃቸው ጠቅላይ ሚኒስትርነት የምትመራው ሃገራቸው ከአውሮፓ ህብረት መነጠሏን ተከትሎ ነው፡፡
ብሪታኒያውያን ከአሁን በኋላ የህብረቱ አባል በሆኑ ሃገራት እንደልባቸው ያለ ቪዛ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ዜግነታቸውን ስለመቀየር እንዲያስቡ አነሳስቷቸዋል፡፡
ከፈረንሳዩ አር.ቲ.ኤል ሬዲዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ስታንሌይ ፈረንሳዊ የመሆን ጉዳይ ሳይሆን የነበረኝን መልሶ የማግኘት ነው ብለዋል በወላጅ እናታቸው በኩል ፈረንሳዊ መሆናቸውን በመጠቆም፡፡
የብሪታኒያን ለ47 ዓመታት የዘለቀ የአባልነት ጉዞ በስተመጨረሻ ለመግታት የቻለው ፖለቲከኛ አባት የሆኑት አዛውንቱ ህብረቱ እ.ኤ.አ በ1973 ሲመሰረት ወደ ቤልጂዬም አቅንተው በብራሰልስ ስራ ከጀመሩ እንግሊዛውያን መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
ለህብረቱ ኮሚሽን ሰርተዋል የህብረቱ ምክር ቤቱ አባል እስከመሆን ደርሰው አገልግለዋልም፡፡
ሃገራቸው ከህብረቱ አባልነት እንድትወጣ ቀስቅሰው የነበረ ቢሆን ከ5 ዓመታት በፊት ብሪታኒያውያን ከህብረቱ ለመውጣት ያላቸውን ፍላጎት በህዝበ ውሳኔ ማረጋገጣቸው ግን ሃሳባቸውን አስቀይሯቸዋል፡፡
“ሁሌ አውሮፓዊ ነኝ” ሲሉ ነው የቀድሞው የሃገሪቱ ወግ አጥባቂ ፓርቲ አባል እና ደራሲ ለአር.ቲ.ኤል የተናገሩት፡፡
አውሮፓ ከህብረቱ በላይ ነው ሲሉም ይናገራሉ፡፡
ዜግነት የመቀየር ፍላጎት እንዳላቸው የታወቀው የልጃቸው የራሽል መጽሃፍ በታተመበት ባሳለፍነው ወርሃ መጋቢት ነው፡፡
ራሽል ሴት አያቷ በፈረንሳይ ቨርሳይልስ መወለዳቸውን በመውሳት አባቷ ፈረንሳዊ ዜግነትን የሚያገኙ ከሆነ እሷም ዜግነቷን ልትቀይር እንደምትችል በመጽሃፏ አስፍራ ነበር፡፡
ቦሪስ ሃገራቸው በድህረ ብሬግዚት ከህብረቱ ጋር ሊኖራት ስለሚችለው የንግድ ግንኙነት ተስማምተዋል፡፡ ስምምነቱ ህግ ሆኖ መጽደቁም ይታወሳል፡፡