እንግሊዝ ዛሬ ምሽት 5፡00 ከአውሮፓ ህብረት ትፋታለች፡፡
ሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከተፈራረቁበት ከ ሶስት ዓመት ተኩል ሂደት በኋላ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት (ብሬግዚት/Brexit) ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት እውን ይሆናል፡፡
በዚህም የሀገሪቱን የ47 ዓመታት የአውሮፓ ህብረት አባልነት ያበቃል፡፡ እንግሊዝ ከህብረቱ መውጣቷን የሚደግፉም ይሁን የሚቃወሙ የሀገሬው ዜጎች ከምሽት 5 ሰዓት በኋላ ስሜታቸውን የሚገልጹ የደስታና የሀዘን ዝግጅቶችን ከወዲሁ ማከናወን ጀምረዋል፡፡
ሀገሪቱ ከህብረቱ ከተፋታች በኋላ የሽግግር ጊዜዋን ትጀምራለች፡፡ የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ከህብረቱ ጋር በፈጸመው ስምምነት መሰረት፣ ለቀጣዮቹ 11 ወራት ሀገሪቱ ከስያሜዋ ነጻነት ውጭ በሁሉም ነገር በህብረቱ አባልነቷ ትቀጥላለች፡፡ የህብረቱን ህግ ትጠብቃለች፤ የበጀት ወጪም ታዋጣለች፡፡
ይሁንና በህብረቱ የሚኖራት ውክልና በነዚህ ወራት እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፡፡ በህብረቱ የመሪዎች ስብሰባ በዚህ የሽግግር ወቅት ባትሳተፍም በህብረቱ የሚወጡ ፖሊሲና ህግጋትን ግን የመጠበቅ ግዴታ አለባት፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንግሊዝ/ዩኬ ከህብረቱ መውጣቷን በማስመልከት ሁነቱ ከመፈጸሙ በፊት ለህዝባቸውና ለህብረቱ አባላት መልእክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው እንግሊዝ ከህብረቱ የምትወጣበትን እለት የአዲስ ብርሀን ጅማሮ አድርገው ለህዝባቸው የድል መልእክት እንደሚያስተላልፉ ነው የተዘገበው፡፡
እለቱ ለህብረቱ መቀመጫ ብራሰልስ አንድ አባሏን ትሸኛለችና አሳዛኝ ይሆንባታል፡፡ የህብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ከሁሉም የአውሮፓ ህብረት ተቋማት ወርዶ ሙዚየም ይገባል፡፡
በዚህ የሽግግር ጊዜ ወደ ሀገሪቱ የሚጓዙ ዜጎች የሚያጋጥማቸው ምንም የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ ምክኒያቱም የሀገሪቱ የጉዞ ህግ የሚመራው በነባሩ የአውሮፓ ህግ መሰረት ነው፡፡ የሀገሬው ዜጎችም በህብረቱ አባል ሀገራት ለ11 ወራት በነጻነት መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡
እኤአ እስከ ታህሳስ 31 በሚዘልቀው የ11 ወራት የሽግግር ጊዜ እንግሊዝ ከህብረቱ ጋር ስለሚኖራት ቀጣይ ግንኙነት ድርድር አድርጋ መጨረስ ይጠበቅባታል፡፡ የሁለቱ አካላት ድርድር መጋቢት 3 በይፋ ይጀምራል፡፡ በድርድሩ ስምምነት ላይ የማይደሩሱ ከሆነ ሁለቱም አካላት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት እንደሚከተላቸው፣ የዚህም ዳፋ ለተቀረው ዓለም እንደሚተርፍ በለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ቀጣይ የንግድ ግንኙነታቸው ዋነኛ የድርድራቸው ነጥብ ይሆናል እንደ ሲኤንኤን ዘገባ፡፡