ፑቲን ከኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ይወያያሉ
የሩሲያ እና ኢራን መሪዎች በቱርክሚኒስታን በወቅታዊው የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ዙሪያ እንደሚመክሩ ተገልጿል
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች በኋላ ከኢራን ጋር ወታደራዊ ግንኙነቷን ማጠናከሯን ምዕራባውያን ይገልጻሉ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከማዕከላዊ እስያ ሀገራት መሪዎች ጋር ለመምከር ቱርክሚኒስታን ገብተዋል።
የኢራኑ አቻቸው መሱድ ፔዝሽኪያንም በጉባኤው ለመሳተፍ አሽጋባት መግባታቸውን የኢራኑ መኸር ኒውስ ዘግቧል።
ቱርክሚኒስታን የ18ኛው ክፍለዘመን ታዋቂው ገጣሚና ምሁር ማግታይሙግሊ ፓረጂ 300ኛ አመት ልደትን ታከብራለች።
ከዚህ ክብረበዓል ባሻገርም የፓኪስታን፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ታጂኪስታን እና ኡዝቤኪስታን መሪዎች የሚሳተፉበትን ጉባኤ ማሰናዳቷ ተገልጿል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት በጉባኤው መክፈቻ ከሞስኮ ወዳጅ እና አጋር ሀገራት ጋር በመሆን “አዲስ የአለም ስርአት” የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ክሬምሊን ገልጿል።
ፑቲን አሜሪካ መራሹና የአንድ ወገን የበላይነት የሚታይበት የአለም ስርአት በባለብዙ ወገን ስርአት እንዲተካ እየሰሩ ሲሆን፥ ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነታቸው ከሻከረው እንደ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ እና ኢራን ጋር ትብብራቸውን በማሳደግ ተጠምደዋል።
ፑቲን በአሽጋባት ቆይታቸው ከኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ ተብሏል።
መሪዎቹ በወቅታዊው የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ዙሪያ እንደሚመክሩም ተገልጿል።
ኢራን በ2022 ለሩሲያ ድሮኖችን ለመላክ የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ስምምነት ከሞስኮ ጋር መፈራረሟን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ ቴህራን አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ለሩሲያ ልካ በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ደጋግመው መግለጻቸው አይዘነጋም።
በጋዛው ጦርነት እስራኤልን የሚያወግዙ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ያወጣችው ሞስኮ በወቅታዊው የእስራኤልና ኢራን ፍጥጫ ዙሪያ ምን አይነት አቋም ትይዛለች የሚለው ይጠበቃል።
የኢራኑ አዲሱ ፕሬዝዳንት በዚህ ወር በሩሲያ በሚደረገው የብሪክስ አባል ሀገራት ሲሳተፉም ከፑቲን ጋር የሀገራቱን ትብብር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ነው የተገለጸው።