የመንግስታቱ ድርጅት እስራኤል የጋዛ የጤና ተቋማትን “ሆን ብላ” አውድማለች አለ
የድርጅቱ መርማሪ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ሪፖርት እስራኤል በጋዛ ሆስፒታሎች ላይ የፈጸምችው ጥቃት በጦር ወንጀል የሚያስጠይቃት ነው ብሏል
እስራኤል የመንግስታቱ ድርጅት የሚያወጣቸው ሪፖርቶች አድሏዊ ናቸው በሚል ስታጣጥል ቆይታለች
እስራኤል በጋዛ ሆስፒታሎች ላይ የፈጸመችው ጥቃት በጦር ወንጀል የሚያስጠይቃት ነው አለ የመንግስታቱ ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን።
ግጭት ባለባቸው ስፍራዎች በማምራት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምረው ኮሚሽኑ፥ እስራኤል “የጋዛ የጤና ስርአትን የማውደም ፖሊሲ ቀርጻ በስፋት ተግብራዋለች” ብሏል።
ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርቱ እስራኤል በጋዛ የጤና ተቋማት ላይ የፈጸመችው ጥቃት እና የታሰሩ ፍልስጤማውያን አያያዟ በጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል የሚመደብ መሆኑን ገልጿል።
ሃማስ እና የፍልስጤም ተዋጊ ሀይሎችም የእስራኤል ታጋቾች ላይ የሚፈጽሙት ተግባር በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ነው የመንግስታቱ ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው።
እስራኤል ለኮሚሽኑ አዲስ ሪፖርት እስካሁን ምላሽ ባትሰጥም ከዚህ ቀደም የመንግስታቱ ድርጅት የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች አድሏዊ ናቸው በሚል ስታጣጥል መቆየቷ ይታወሳል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ለመግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርበውን የምርመራ ሪፖርት በመንግስታቱ ድርጅት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ሃላፊ ናቪ ፒሌይ መርተርታል።
የእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች “የጤና ባለሙያዎችን ሆን ብለው ገድለዋል፤ አስረዋል፤ አሰቃይተዋል” ያለው ሪፖርቱ፥ በተለይ ህጻናት በጤና ስርአቱ መውደቅ ክፉኛ መጎዳታቸውን አብራርቷል።
ኮሚሽኑ የአምስት አመቷን ሂንድ ራጃብ አሟሟት ዋቢ አድርጎ ጠቅሷል። ከቤተሰቦቿ ጋር የእስራኤልን ጥቃት ስትሸሽ መኪናቸው ይመታል። አብዛኞቹ የቤተሰብ አባላት ህይወታቸው ወዲያውኑ ሲያልፍ ሂንድ የፍልስጤም ቀይ መስቀል በፍጥነት እንዲደርስላት ትጠይቃለች። የቀይ መስቀል አምቡላንስ ለሂንድ ለመድረስ በጉዞ ላይ እንዳለ ግን በሌላ ጥቃት ተመቶ ሁሉም ህይወታቸው አልፏል።
የተመድ የመርማሪ ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ የጤና ተቋማት ላይ ያደረሰችው ውድመት በፍልስጤማውያን መጻኢ በተለይ በህጻናት ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሏል ይላል።
ሪፖርቱ ሃማስን ጨምሮ ነፍጥ ያነገቡ የፍልስጤም ቡድኖች ከእስራኤል ታግተው በተወሰዱ ሰዎች ላይ “አካላዊ እና ጾታዊ ጥቃት” እያደረሱ መሆኑንና ታጋቾቹ የውሃ፣ ምግብና ንጽህና መጠበቂያ እንዲያጡ መደረጉን ጠቅሷል።
በጋዛ የሚገኙ ታጋቾች ያለምንም ቅድመሁኔታ ይለቀቁ ያለው የተመድ መርማሪ ኮሚሽን፥ በእስራኤል እስርቤቶች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሁኔታም አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።
የእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች ፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ ከባድ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈር እና የተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶችን እያደረሱ መሆኑን በመጥቀስም ጥቃቱ በሀገሪቱ የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢራማር ቤን ግቪር “ቀጥተኛ ትዕዛዝ” እንደሚፈጸም አብራርቷል።
የኮሚሽኑ ሪፖርት እስራኤል በአለማቀፉ የፍትህ ፍርድቤት (አይሲጄ) እና በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት የቀረቡባትን ክሶች የሚያጠናክሩ በርካታ ማስረጃዎችን መያዙንም ቢቢሲ ዘግቧል።