ቴስላ ሙሉ በሙሉ ያለ አሽከርካሪ በራሱ የሚንቀሳቀስ ሳይበርካፕ የተባለ አዲስ መኪና አስተዋወቀ
አዲሱ መኪና መሪም ሆነ የነዳጅ መስጫ እና የፍጥነት መቆጣጠርያ ፔዳል እንደሌለው ታውቋል
ኢለን መስክ መኪናው በሰዎች ከሚነዱት 10 እና 20 እጥፍ አደጋ የማድረስ እድላቸው ዝቅተኛ ነው ብሏል
የቴስላ ኩባያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ሳይበርካፕ የተሰኝ አዲስ ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀስ መኪና አስተዋውቋል፡፡
በትላንትናው እለት የአዲሱ ተሸከርካሪ ፕሮቶታይፕ በዋርነር ብሮስ ስቱድዮ ግቢ ውስጥ ለእይታ ይፋ ያደረገው ኢለን ሳይበርካፕ ወይም ሮቦታክሲ የተባለው አዲስ መኪና በታክሲ አገልግሎት ላይ እንደሚሰማራ ገልጿል፡፡
በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ሰዎች ከሚያሽከረክሯቸው መኪኖች ደህንነታቸው ከ10 እና 20 በመቶ እንደሚሻሉ የተናገረው መስክ በሰዎች ላይ የሚደርስ ሞት እና ጉዳትን ለመቀነስ እንደሚያግዙ አብራርቷል፡፡
ሆኖም ተሸከርካሪው አሁን በሚገኝበት አቋም ላይ ከመድረሱ በፊት በሙከራ ወቅት ከ13 ጊዜ በላይ አደገኛ ግጭቶች እንዳጋጠሙት ተሰምቷል፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀመው ሳይበርካፕ በሁሉም አቅጣጫዎች በተገጠሙለት ካሜራዎች እና ኢንድ ቱ ኢንድ የተባለውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በአካባቢው የሚገኙ የመንገድ ምስሎችን በመሰብሰብ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል፡፡
መኪኖቹ ለገበያ ሲቀርቡ ከ30 ሺህ ዶላር ያነሰ ዋጋ የሚቆረጥላቸው ሲሆን የተሽከርካሪው አማካኝ የሥራ ማስኬጃ ዋጋ 0.20 ዶላር መሆኑ ሲነገር በ2026 ወደ ምርት ይገባል ተብሏል፡፡
ተሸከርካሪው ከሰዎች ንክኪ ውጭ በራሱ መንቀሳቀስ መቻሉ የመኪናው ባለቤቶች ስራ መስራት ሳይጠበቅባቸው የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ገቢ መሰብሰብ እንደሚችልም ዩሮ ኒውስ አስነብቧል፡፡
ኢለን መስክ ተሸከርካሪው በሙሉ አቅም እንዳይንቀሳቀስ እና እንዳይሰራ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል በቂ የሃይል መሙያ መሰረተ ልማቶች አለመሟላት ዋነኛው ነው፡፡
ሌላው ደግሞ የአሜሪካ ግዛቶች ራሳቸውን ከሚያሽከረክሩ ተሸከርካሪዎች ጋር በተያያዘ የሚከተሉት የተለያየ ህግ ይጠቀሳል፡፡
አንዳንድ ግዛቶች ከሰው ንክኪ የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቢፈቅዱም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ መኪናውን እንዲቆጣጠር ሾፌሩ በቦታው እንዲቀመጥ ያዛሉ፡፡
ሌሎች ደግሞ ተሸከርካሪዎቹ የሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የተለዩ እንዲሆን አድርገዋል፡፡
በ2027 ወደ ገበያ እንደሚገባ የሚጠበቀው የታክሲ አገልግሎት የሚሰጠው የቴስላ ተሸከርካሪ አሁን ካሉ የግዛት ህጎች ጋር በተያያዘ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዳይገባ እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡