በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምክንያት ልንማራቸው የማይገቡ ሙያዎች የትኞቹ ናቸው?
ከ10 በላይ የዓለማችን ሙያዎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምክንያት ከገበያ ውጪ እየሆኑ ነው ተብሏል
የቴክኖሎጂ ሙያዎች የበለጠ ገበያ የደራላቸው የሙያ መስኮች እንደሆኑ ተገልጿል
የዓለማችን ቴክኖሎጂ በየጊዜው የበለጠ እየዘመኑ መምጣታቸውን ተከትሎ የሰው ልጆችን ህይወት የበለጠ እያቀለሉ ይገኛሉ፡፡
በዚያው ልክ ግን ከዚህ በፊት በሰው ልጆች ተይዘው የነበሩ ስራዎችን በቴክኖሎጂ እየተተኩ መምጣታቸው የሰዎችን ህይወት ከማቅለል ጎን ለጎን እያከበዱም ይገኛሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የአርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ስራዎች እየዘመኑና ቴክኖሎጂዎቹ ያለ እረፍት ስራዎችን ማከናወን መቻላቸውን ተከትሎ ብዙ ስራዎች ከሰው ልጆች እጅ እየወጡ ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት በአርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ከሚተኩ ስራዎች መካከል ጸሀፊነት፣ መረጃ ትንተና፣ መረጃ ማደራጀት፣ የዲዛይን ስራ (ዲዛይኒንግ) እና የምስል አርትኦት (ቪዲዮ ኢዲቲንግ) ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሙያዎች በአርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የሚሸፈኑ በመሆናቸው የሰው ልጆች መማር የማይጠበቅባቸው ሙያዎች ናቸው ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
እነዚህ ስራዎች በቴክኖሎጂዎች ይሸፈናሉ ቢባልም ሙሉ ለሙሉ የሰው ልጆች አያስፈልጉም ተብሎ ሊደመደም እንደማይችል ግን ያነሳል።
የቴክኖሎጂ እና ምህንድስና ሙያዎች በቀጣዮቹ ዓመታት እጅግ ተፈላጊ የሙያ መስኮች ሆነው እንደሚቀጥሉም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም ሰው ሰራሽ አስተውሎት በቀጣይ እስከ 300 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎችን ስራ እንደሚነጥቅ ጥናቶች ያመላክታሉ።