በዚህ መተግበሪያ መሰረት ሰዎች ከፈለጉ ከሴጣንም ጋር ማውራት ይችላሉ ተብሏል
የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከኢየሱስ ጋር ቻት ማድረጊያ አፕ መስራቱን ገለጸ፡፡
ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ያደረገው ካት ሉፍ ሶፍትዌር ኩባንያ ሰዎች ከእየሱስ ጋር በጽሁፍ መልዕክት ማውራት የሚያስችል መተግበሪያ መስራቱን አስታውቋል፡፡
ቻትጅቢቲ የተሰኘው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሰራው ይህ አፕ ወይም መተግበሪያ ሰዎች እየሱስ ክርስቶስን ጨምሮ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው ከተጠቀሱ አካላት ጋርም ማውራት ያስችላል ተብሏል፡፡
መተግበሪያው አማኞች በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው እና ታሪካቸው ከተጠቀሱ አካላት ጋር ስማቸውን እየጠቀሱ እንዲወያዩ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
መተግበሪያው ሰዎች ከእየሱስ በተጨማሪ ከሴጣን፣ ይሁዳ፣ አብርሃም እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ጻድቃን ጋር እንዲያወሩ ተደርጎ መበልጸጉ ተገልጿል፡፡
- "እየሱስን ለማግኘት" ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 80 ኡጋንዳዊያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
- “ኢየሱስን ለማየት ተራቡ” በሚል 58 ሰዎች ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገው ፓስተር ተያዘ
መተግበሪያው ለተጠቃሚዎች ይፋ መደረጉን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆን አንዳንዶች ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
የሶፍትዌሩ አበልጻጊ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ስቴፈን ፒተር እንዳሉት መተግበሪያውን ቀለል አድርገን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ያለማነው ነው ብለዋል፡፡
ይህን ቴክኖሎጂ ማልማት አንድ ነገር ቢሆንም የሀይማኖቱ አማኞች የጠበቁት ያልሆነላቸው እና ደስተኛ ያልሆኑ አማኞች አሉ ማለታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
በተለይም በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ የተወሰኑ አካላት ማንነታቸው የተገለጸበት መንገድ እና በመተግበሪያው ላይ ያላቸው ምላሽ ተመሳሳይ እንዳልሆነም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱ አካላትን ወደ ዚህ መተግበሪያው ስናመጣ ማስተካከያዎችን እንዳደረጉ የገለጹት ስራ አስኪያጁ በተለይም የጾታ ተፈጥሯዊ አመለካከቶችን ፣ የንግግር ዘዬ እና ተያያዥ የሆኑ ማንነቶች ላይ ጥንቃቄ አድርገናል ብለዋል፡፡
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ መተግበሪያው የተሰራው የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን አስተያየት ባካተተ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መጽሃፍ ቅዱስን የተረዳ እና በዛ ልክ መግባባት በሚያስችል መልኩ ነው፡፡
ይህ መተግበሪያ በየጊዜው እየዳበረ እና የሰዎችን አስተያየት በመቀበል እየተሻሻለ ይሄዳል የተባለ ሲሆን የተወሰኑ አገልግሎቶች በወር እስከ 3 ዶላር ክፍያን ይጠይቃሉ፡፡