“ኢየሱስን ለማየት ተራቡ” በሚል 58 ሰዎች ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገው ፓስተር ተያዘ
ተጨማሪ ህይወታችው ያለፈ ሰዎች ካሉ ለማግኘትም ፍለጋው መቀጠሉ ተገልጿል
በአሰሳ የተገኙት ሰዎችም ምግብና መጠጥ በፍጹም አንወስድም እያሉ መሆናቸው የሟቾቹን ቁጥር ከፍ እንዳያደርገው ስጋት ፈጥሯል
በኬንያ ምስራቃዊ ክፍል ማሊንዲ በተሰኘችው ከተማ “ከተራባችሁ ከኢየሱስ ጋር ትገናኛላችሁ፤ ገነትም ትገባላችሁ” የሚል አስተምሮ ይዞ የመጣ ፓስተር የ58 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ተነግሯል።
በጫካ ውስጥ ተደብቀው ራሳቸውን ከምግብና ከውሃ አርቀው የተባሉትን ሲጠባበቁ የነበሩና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ፍለጋውም ቀጥሎ ትናንት የ26ቱ አስከሬን ተገኝቷል።
የማሊንዲ ከተማ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ሃላፊው ቻርለስ ካማኡ ግን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችልና ፍለጋና ቁፋሮው መቀጠሉን ገልጸዋል።
ቀደም ብሎ የ47 ሰዎች ህይወት ማለፉ የተነገረ ሲሆን ዛሬ ከስአት በኋላ በወጡ ዘገባዎች የሟቾቹ ቁጥር ወደ 58 ከፍ ማለቱን አመላክተዋል ብሏል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው።
ከሞቱት ባሻገርም በጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ በመራብ ውስጥ ፈጣሪያቸውን ለመመልከት የሚጠባበቁ በርካታ ሰዎች እንደሚኖሩ ነው የተገለጸው።
የኬንያ ቀይመስቀልም 112 ሰዎች የገቡበት አይታወቅም ያለ ሲሆን፥ በጫካ ውስጥ ተደብቀው እየጾሙ የፈጣሪያቸውን መምጣት የሚጠባበቁ ሰዎችን ፍለጋው ቀጥሏል ተብሏል።
በአሰሳ የተገኙት ሰዎችም ምግብና መጠጥ በፍጹም አንወስድም እያሉ መሆናቸው የሟቾቹን ቁጥር ከፍ እንዳያደርገው ስጋት ፈጥሯል።
325 ሄክታር የሚሸፍነው ሻካሆላ የተሰኘው ጫካን እጅግ ሰፊ መሆኑ ግን የፍለጋ ስራውን ረጅም እንደሚያደርገው ነው የሚጠበቀው።
የኬንያ ፖሊስ የዚህን ሁሉ ችግር ምንጭ የ“ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቸርች” መስራች ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገበት እንደሚገኝ ተገልጿል።
ፓስተሩ ባለፈው ወርም በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ቢሆንም በ100 ሺህ የኬንያ ሽልንግ ወይም 700 ዶላር ዋስ መለቀቁን የአካባቢውን መገናኛ ብዙሃን ጠቅሶ ፍራንስ24 ዘግቧል።
ንቴንጌ ከስድስት ተከታዮቹ ጋር በድጋሚ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው ስለመጀመሩም ነው ዘገባው ያከለው።
የመብት ተሟጋቾች አሁንም የፓስተሩን አስተምሮ የሚከተሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንና መንግስት በጫካ ውስጥ የተደበቁትን ፈጥኖ ደርሶ ካልታደጋቸው ህይወታቸውን የሚያጡት ቁጥር ሊያሳቅብ እንደሚችል ገልጸዋል።
የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ኪቱሪ ኪንዲኪ በበኩላቸው፥ በቂ የጸጥታ ሃይሎች ወደ “ሻካሆላ” ጫካ መላካቸውንና ፍለጋውም ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በነገው እለትም “የሞት ጫካ” ሲሉ ወደገለጹት አካባቢ እንደሚያመሩ ነው ያነሱት።
የሃይማኖት ነጻነትን እንደሽፋን በመጠቀም በአሳሳች አስተምህሮ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት የሚነጥቁ አካላት “የከፋ ቅጣት” ይጠብቃቸዋልም ብለዋል።