80 ከመቶ ሴት ሰራተኞች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስራቸውን ሊነጠቁ ይችላል ተባለ
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂው ሴቶች ይበልጥ ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ተገልጿል
300 ሚሊዮን የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስራቸውን ሊነጠቁ እንደሚችሉ ጥናት አመላክቷል
አርቲፊሻል ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየዘመነ የመጣ ሲሆን አሁን ላይ በሰዎች ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን ሳይቀር በመቆጣጠር ላይ ነው፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ የሰዎችን ህይወት ቀላል ቢያደርግም በርካታ ስራዎችን እየተቆጣጠረ መምጣቱ የሰው ልጆችን አላስፈላጊነት እያሰፋ መጥቷል ተብሏል፡፡
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሁለቱንም ጾታዎች የሚጎዳ ቢሆንም በተለይ ሴቶችን የበለጠ ይጎዳል የተባለ ሲሆን ቴክኖሎጂው እስከ 80 በመቶ በሴቶች ይሰሩ የነበሩ ስራዎችን ይቆጣጠራል ተብሏል፡፡
ዩሮ ኒውስ በኬናን-ፍላገር በተሰኘው የጥናት ተቋም የተሰራ ጥናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስራቸውን ይነጠቃሉ፡፡
በአውሮፓና አሜሪካ ጉልበትን በሚጠይቁና በቢሮ ስራዎች ላይ የሚገኙ ወንዶች ቁጥር መሳ ለመሳ ነው፤ ማለትም 50 ከመቶው በቢሮ ቀሪው 50 ከመቶ ደግሞ ጉልበት በሚጠይቁ ስራዎች ላይ ናቸው።
በቢሮ ውስጥ ስራ የሴቶች ድርሻ ከፍ ያለ ነው፤ 70 ከመቶ ሴቶች ጉልበት በማይጠይቁ የቢሮ ውስጥ ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል።
በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ሴት ሰራተኞች በአርቲፊሻል ኢንጀለጀንስ ስራቸውን የመነጠቅ እድላቸው ይሰፋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካውየኢንቨስትመንት ባንክ ጎልድማን ሳችስ በአሜሪካ እና አውሮፓ ብቻ 300 ሚሊዮን የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስራቸውን እንደሚነጠቁ የሚያመላክት ጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የቢሮ አስተዳድር፣ የጤና ማማከር፣ የጸህፈት፣ ሂሳብ ምዝገባ፣ ትርጉም እና ሌሎች የአገልግሎት ስራ መስኮች በዚህ ቴክኖሎጂ በመተካት ላይ ያሉ የስራ ዘርፎች ናቸው ተብሏል፡፡
በርካታ የዓለማችን ጠበብቶች የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የፈጠራ ውጤቶች የሰው ልጆችን እስከ ማጥፋት የሚደርሱ ጉዳቶችን ሊያደርስ ይችላሉ ሲሉ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡
እጅግ ሰፊ ጊዜ የሚጠይቁ እና አድካሚ ስራዎች እያቀለለ የአለምን እድገት ያፋጥናል በሚል የሚከራከሩም አሉ።