አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የአለማችን 40 በመቶ ሰራተኞች ስራ ሊያሳጣ እንደሚችል ተነገረ
የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ይፋ ያደረገው ጥናት ቴክኖሎጂው በሀገራት መካከል የእድገት ልዩነቱን እያሰፋው ይሄዳል ብሏል
አርቲፊሻል ኢንተርለጀንስ በዳቮስ እየተካሄደ በሚገኘው የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ዋነኛ የምክክር አጀንዳ ሆኗል
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የአለማችን 40 በመቶ ሰራተኞችን ስራ ሊነጥቅ እንደሚችል የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ገለጸ።
ተቋሙ ይፋ ባደረገው አዲስ ጥናት ቴክኖሎጂው ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ተንብዩዋል።
የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጂየቫ “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) የሰው ልጆችን ስራ ከመንጠቅ ባሻገር ኢፍትሃዊነትን ያባብሳል” ብለዋል።
ቴክኖሎጂው ከባድ ማህበራዊ ቀውስ ከማስከተሉ በፊትም ፖሊሲ አውጪዎች መፍትሄዎችን እንዲያዘጋጁ ነው ያሳሰቡት።
በዳቮስ እየተካሄደ በሚገኘው የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ይሄው የሰው ልጆችን ስራ ይነጥቃል የሚል ስጋት የቀረበበት አርቲፊሻል ኢንተርለጀንስ ዋነኛ የምክክር አጀንዳ ሆኗል።
የአለም የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በዚሁ ስብሰባ ይፋ ያደረገው ጥናትም ቴክኖሎጂውን በስፋት መጠቅም የሚያስችል መሰረተ ልማት በዘረጉት የበለጸጉት ሀገራት ሰው ሰራሽ አስተውሎት እስከ 60 በመቶ ሰራተኞች ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል ብሏል።
ቴክኖሎጂው በታዳጊ ሀገራት ደግሞ 26 በመቶ ስራዎች ላይ ተጽዕኖው ሊያሳርፍ አልያም ስራን ሊነጥቅ እንደሚችል በአይኤምኤፍ ተገምቷል።
ባደጉትና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት መካከል ያለው ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ የማዋል ልዩነት የሀገራቱን የእድገት ልዩነት እያሰፋው እንደሚሄድ ነው የሚጠበቀው።
ቴክኖሎጂው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እና ረጅም አመት ያገለገሉ ሰራተኞችን ከስራ በማሰናበት ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል ከወዲሁ ዝግጅት ይደረግ ሲል ነው አይኤምኤፍ ያሳሰበው።
የበለጸጉት ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ይዞት ከመጣው በረከት በብዙው ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ቢጠበቅም ሚሊየኖች ከስራ ገበታቸው ሊሰናበቱ ይችላሉ የሚሉ ጥናቶች በተደጋጋሚ ወጥተዋል።
በዳቮሱ ምክክር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምን ያህል ስራን እያቀለለ እና ውጤታማነትን እያሳደገ እንደሚገኝ ቢነሳበትም ስጋቱ አይሏል።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ባለፈው ወር የመጀመሪያውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቁጥጥር ህግ ማጽደቃቸው ይታወሳል።
በያዝነው የፈረንጆቹ አመት በህብረቱ ፓርላማ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ህግ በዘርፉ የሚደረገውን ፉክክር ጤናማ ከማድረግ ባለፈ ተጠያቂነትን ያሰፍናል ተብሏል።
አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ቻይናም የራሳቸውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቁጥጥር ህግ ለማጽደቅ በሂደት ላይ ናቸው።