የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂው የህክምና ማስረጃዎችን መሰረት አድርጎ ነው ትንበያ የሚሰጠው
ተመራማሪዎች የሰው ልጆችን የመሞቻ ጊዜ የሚተነብይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፈጥረናል አሉ።
የአሜሪካና ዴንማርክ ተመራማሪዎች ያስተዋወቁት “Life2vec” የተሰኘ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስርአት የሰዎችን አጠቃላይ መረጃ እንዲያጠና ተደርጎ ነው ትንበያውን የሚሰጠው።
የልደት ቀን፣ የትምህርት ቤት ታሪክ፣ ደመወዝ፣ የቤትና ጤና ሁኔታን እንዲያጠና የተደረገው “Life2vec”፥ ከዴንማርክ የጤናና ስነህዝብ ተቋማት የተገኙ የ6 ሚሊየን ሰዎች መረጃዎች ተጭነውበታል።
በእነዚህ መረጃዎች መሰረትም የሰዎችን የመሞቻ ጊዜ የሚተነብየው ይህ ቴክኖሎጂ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ነው ተመራማሪዎቹ የተናገሩት።
ከ2016 እስከ 2020 ባሉት አምስት አመታት በህይወት ያሉና የሌሉ እድሜያቸው ከ35 እስከ 65 የሆኑ ሰዎችን መረጃ በመስጠት ማን እንደሚሞትና ማን በህይወት እንደሚቆይ እንዲተነብይ ተደርጓል።
በዚህም የቴክኖሎጂው ትንበያ 78 በመቶ ትክክለኛ ሆኖ ተገኝቷል ይላሉ ተመራማሪዎቹ።
የጥናቱ መሪ ፕሮፌሰር ሱኔ ሌህማን እንደሚሉት “Life2vec” እንዲሰለጥን የተደረገው (መረጃ የተሞላበት) በዴንማርክ ብቻ በመሆኑ በሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ውጤት ላያስገኝ ይችላል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስርአቱ በተደራጀ መረጃ ከሰለጠነ በሌሎች ሀገራትም የተሳካ ትንበያ ሊሰጥ እንደሚችል አብራርተዋል።
ቴክኖሎጂው የሚሰጠው ትንበያ ከድንገተኛ ሞት ሊጠብቅ እንደሚችል የሚያነሱት ፕሮፌሰር ሱኔ፥ በኢንሹራንስ እና መሰል ኩባንያዎች እጅ ከገባ ግን መልሶ እኛኑ የሚጎዳ ነው ባይ ናቸው።
“Life2vec” በአሁኑ ወቅት ግለሰቦች እንዲጠቀሙበት አልተለቀቀም።
ይሁን እንጂ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሰል የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።